ኢትዮጵያ ከሰሞኑ በወታደራዊ ትርዒት ላይ ያሳየችው “SH-15” ዘመናዊ መድፍ እውነታዎች
አዋሽ አርባ በታሄደ ወታደራዊ ትሪዒት የታዩት ዘመናዊ መድፎች የበርካቶችን ቀልብ ስበዋል
“SH-15” ቻይና ሰራሽ መድፍ በሰዓት እስከ 90 ኪ.ሜ የሚከንፍ ሲሆን፤ እስከ 53 ኪ.ሜ ርቀት የሚገኝ ኢላማን ይመታል
በኢትዮጵያ ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደ ወታደራዊ ትርዒት ላይ የታዩ ዘመናዊ ባለ ተሸከርካሪ መድፎች የበረካቶችን ቀልብ ስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት በአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት በመገኘት በአየር ኃይልና በሜካናይዝድ ተቀናጅቶ የተካሄደውን የጥምር ጦር ወታደራዊ ትሪዒት መመልከታቸው ይታወሳል።
ታዲያ በዚህ ትርዒት ላይ የበርካቶችን ቀልብ የሳበ የጦር መሳሪያዎች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ባለ ተሸከርካሪው መድፍ አንዱ ነበር።
ይህ የጦር መሳሪያ “SH-15” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ተሸከርካሪ ላይ የተገጠመ መድፍ ሲሆን፤ የቻይና ስሪት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
መድፉ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንጆቹ 2017 በቻይና የተዋወቀ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2018 አና 2019 ወደ ውጊያ ስምሪት መግባቱም ተነግሯል።
ዋናው መሳሪያ (Main gun) 155 mm ሲሆን፤ የባሬሉ ርዝመት ድግሞ 52 ካሊበርስ ነው፤ SH-15 ባለ ተሸከርካሪ መድፍ 1x12.7 mm ማሽን ገን የተገጠመለትም ነው።
መድፉ በአማካይ እስከ 53 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ የጠላት ኢላማን መምነታት የሚችል መሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
SH-15 በኮምፒውተር የታገዘ የመድፍ ተኩስ ቁጥጥር ስርዓት፣ አሰሳ፣ አቀማመጥ እና ዒላማ አድራጊ ስርዓቶች የተገጠመለት ሲሆን፤ የኢላማ መረጃን ከመድፍ ትዝኣዝ ሰጪ መኪና ይቀበላል።
መድፉ ሻንዚ የተባለ ዘመናዊ ወታደራዊ መኪናው ላይ የተገጠመ ሲሆን፤ መኪናው 6 መድፈኛ ወታደሮችን የመጫን አቅም ያለው እንደሆነም ነው የተነገረው።
ተሸከርካሪው ብረት ለበስ ሲሆን፤ ይህም ወታደሮቹን ከጥቃቅን የጦር መሳሪያዎች እና ከመድፍ ፍንጣሪ የመከላከል አቅምን አላብሶታል።
SH-15 ባለ ተሸከርካሪ መድፍ በሰዓት 90 ኪሎ ሜትር ድረስ መክነፍ ይችላል የተባለ ሲሆን፤ በአንድ ጊዜም እስከ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ማዳረስ ይችላል።
ባለ 52 ባረል መድፉ የ 6×6 ተሽከርካሪ የሆነ ልዩ ሰስፔንሽን ስርዓት የተገጠመለት ሲሆን፤ ይህም የመድፉን ትክክለኛት የተሸለ እንደሚያደርገው ተነግሯል።
ከዚህ ቀደም ፓኪስታን ለግዢ ካዘዘችው መረጃ ላይ እንደተገኘው ከሆነ የአንዱ SH-15 ባለ ተሸከርካሪ መድፍ 2 ነጠብ 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደነበረ ዲፌንስ ፖስት በድረ ገጹ አስታውቋል።