ዕለቱ “አልረሳውም፤ እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ” በሚል መሪ ሃሳብ ይታሰባል ተብሏል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር የፈረጀው ህወሃት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን መንግስት ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ ዕለቱ በዚህ ዓመት ታስቦ እንደሚወል ተገለጸ፡፡
የመንግስት ኮሙኑኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ህወሃት የመከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት መፈጸሙን አስታውሶ ፤ ቡድኑ ይህንንም ያደረገው ሀገር ለማፍረስ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ይህንን ዕለትም የኢትዮጵያ መንግስት በልዩ ሁኔታ አስቦት እንደሚውል ነው የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ ያስታወቀው፡፡
ህግ ማስከበር ዘመቻው ተጠናቋል መባሉን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ነው
አገልግሎቱ “የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን ለመንካት በሽብር ቡድኑ የተወሰደው እርምጃ መቼም የሚረሳ ባለመሆኑ ይህ ቀን በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታስቦ ይውላል” ያለ ሲሆን ዕለቱ መከላከያ ሰራዊቱ ከፍ ብሎ የሚታሰብበት ይሆናል ብሏል፡፡
ኢትዮጵያውያን ቀኑን ሲያስቡ “አልረሳውም! እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ!” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ሕዝቡ፤ በሰራዊቱ ላይ የተፈጸመውን ግፍ አይረሳም ያለው አገልገሎቱ “እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስክ ሰራዊት ነኝ” በሚል እንዲሰለፍ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሁሉም ዘርፍ ተደራጅተው ሀገራቸውን ከአደጋ እንዲጠብቁም መንግስት ጠይቋል፡፡
“የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል”
ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት ያሉ ሰራተኞች እና ማህበረሰቡ አንድ ላይ በመሆን ለ45 ሰኮንዶች እጃቸውን ደረታቸው ላይ አድርገው አስበው እንዲቆዩም ይደረጋል ተብሏል፡፡
ህወሓት በቃል አቀባዩ በኩል በሰራዊቱ ላይ “መብረቃዊ” ያለውን የ45 ደቂቃ ጥቃት እንደፈጸመ ማስታወቁን ያስታወሰው አገልግሎቱ በዕለቱ የደም ልገሳና የሻማ ማብራት ፕሮግራም እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡
በወቅቱ የህወሃት ቃል አቀባይ የነበረው ሴኩቱሬ ጌታቸው በሰራዊቱ ላይ “መብረቃዊ ጥቃት” መፈጻማቸውን ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋር በነበረው ቆይታ መግለጹ ይታወሳል፡፡