ከህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውጪ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን መልሶ መመዝገብ የሚያስችል የህግ ማሻሻያ ፀደቀ
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ አጽድቋል
ህወሓት ያቀረበው የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ በተሸሻለው አዋጅ ምላሽ ያገኛል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውጪ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን መልሶ መመዝገብ የሚያስችል የህግ ማሻሻያ አፀደቀ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር የማሻሻያ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው አርብ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባው ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበ አዋጅ ላይ መወያየቱ ይታወሳል።
- የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችን መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት እንዲዘረጋ ወሰነ
- ምርጫ ቦርድ ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያሰችል የህግ አግባብ የለም አለ
በዚህም የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ረቂቅ የአዋጅ ማሸሻያ ተዘጋጅቶ የቀረበለት ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ይታወቃል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው አርብ የተላከለትን ቤት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በተመራለት በ3 ቀናት ውስጥ ነው ተቀብሎ ያጻቀው።
በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የማሻሻያ አዋጁ ዙሪያ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብሪያ “እስካሁን በነበረው ሥርዓት የፖለቲካ ባህላችን ደካማ በመሆኑ የግጭትና የጦርነት አዙሪት ውስጥ እየከተተን ቆይቷል” ብለዋል።
አቶ ተስፋዬ በማብራሪያቸውም፤ የአዋጁ መሻሻል በትጥቅ ትግል ስልጣን መያዝ የሚፈልጉ ሃይሎች ህጋዊና ሰላማዊ አማራጭን እንዲከተሉ የሚያደርግ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
“በሃይልና በጠመንጃ ችግሮችን ለመፍታት መሞከር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል” ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ መንግስት ለሰላማዊ አማራጮች በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ባህልን ለማሳደግ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻልና በትጥቅ ትግል የሚሳተፉ ቡድኖች ወደ ህጋዊ መንገድ እንዲመጡ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርም አንዱ ትኩረት መሆኑን አንስተዋል።
ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላም የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር የማሻሻያ አዋጅ በ2 ተቃውሞ በ1 ድምፀ ታዕቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያሰችል የህግ አግባብ ባለመኖሩ ህወሓት ያቀረበውን የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ አለመቀበሉ ይታወሳል።
ለቦርዱ ውሳኔ ምክንያት የሆነው ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር አሁን ባይኖርም እንደገና ህጋዊ ሰውነቱን ለፓርቲው ለመመለስ የሚያችሉ ድንጋጌዎች በአዋጅ 1662/2011 ተደንግጎ ባለመገኘቱ ነው ቦርዱ በወቅቱ ውሳኔውን ያሳለፈው።
ምርጫ ቦርድ ህወሓት ያቀረበውን የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ በህግ አግባብ እንደማይቀበለው በመግለጽ፤ ህወሓት ህጋዊ ሰውነት የሚያገኘው በድጋሚ ለመመዝገብ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሲፈቅድ ነው ማለቱም አይዘነጋም።
በዛሬው እለት የፀደቀው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር ማሻሻያ ህወሓት ያቀረበውን የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ ምለሽ የሚያስገኝ ነው።