የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን ለማረጋገጥ እየሰራን ነው ብሏል
ኢትዮጵያ አጣች ስለተባለው በሶማሊ ላንድ የበርበራ ወደብ ጉዳይ እያጣራች መሆኑን ገለጸች፡፡
ስለ ጉዳዩ እያጣራን ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ዛሬ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የጉዳዩን እውነትነት ለማረጋገጥ እያጣራን ነው ሲሉ መልሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሶማሊ ላንድ መንግስት በወደቡ ላይ የሚኖር የባለቤትነት መብትን አስመልክቶ ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ማሟላት ባለመቻሏ ነው የባለቤትነት መብቷን ማጣቷ ተነግሯል፡፡
የሃገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ማሟላት የነበረበትን የባለቤትነት መስፈርቶች በጊዜው ባለሟሟላቱ ባለቤትነቱን ተነጥቋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ከቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ለወደቡ ግንባታ የተቀመጠውን የገንዘብ መዋጮ መክፈል ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ይህን በወቅቱ አላደረገችም።
ኢትዮጵያ በወደቡ የ19 በመቶ ድርሻ ማግኘቷን ተከትሎ መርከብ ማሰማራት ጀምራ እንደነበርና ጊቤ የተባለችው የጭነት መርከብ ከወደቡ ደርሳ ጭነት ማራገፏን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።
የወደቡ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ የኮንቴይነር ተርሚናል የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ እና የዲፒ ወርልድ ዳይሬክተር ሱልጣን ቢን ሱለይማን በተገኙበት ከወራት በፊት ተመርቆ በይፋ ስራ መጀመሩም የሚታወስ ነው።
ወጪና ገቢ ዕቃዎቿን ከምታጓጉዝበት ጅቡቲ ወደብ ባለፈ አማራጭ ወደቦችን በማማተር ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን በአማራጭነት ለመጠቀም ትፈልጋለች፡፡
የወደቡ 51 በመቶ ድርሻ በአረብ ኤሚሬቱ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክ ተቋም ዲ ፒ ወርልድ፤ 30 በመቶ ደግሞ በራሷ በባለቤቷ በሶማሌላንድ የተያዘ ነው፡፡ ቀሪው 19 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ የተያዘ ነበር።
ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን መጠቀሟና ቀጠናዊ አንድምታው
በጋዜጣዊ መግለጫቸው ሱዳን ያለ አግባብ በድንበር አካባቢ ስለምታደርገው እንቅስቃሴና ስለያዘቻቸው መሬቶች ያብራሩት አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ እንቅስቃሴው የሱዳናውያን ፍላጎት ነው ብላ እንደማታምንና ነገሩን ላለማጋጋል ጥረት እያደረገች መሆኑን በመጠቆም እንደሚቆም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከሳምንት በፊት የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም አስመልክተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ "በሱዳን የተወሰደው ግዛታችን በየትኛውም መመዘኛ ይመለሳል" ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ሆኖም ሱዳን ንግግሩ የተሳሳተ እንደሆነ በመግለጽና በማውገዝ መግለጫ ማውጣቷ አይዘነጋም፡፡
የትግራይ ህዝብ እስከፈለገው ድረስ እርዳታ ማጓጓዙ እንደሚቀጥል የተናገሩት አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ ምስራቅ፣ ምዕራብ የሚል ክፍፍል ውስጥ ሳትገባ ብሔራዊ ጥቅሟን መነሻ አድርጋ የዐረብ ሃገራትን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራም ገልጸዋል፡፡