የትግራይ ታጣቂዎች ከጦር ግንባሮች ለቀው መውጣት መጀመራቸው ተገለጸ
"የትግራይ ታጣቂዎች" ጥትቅ የሚፈቱበት ዝርዝር ዕቅድ ላይ የሚሰራ የባለሞያዎች የጋራ ኮሚቴ ሽሬ ላይ እየመከረ ነው
ታጣቂዎቹ ከማይ ቅነጣል፣ ዛላምበሳ፣ ነበለት፣ ጨርጨር፣ ኩኩፍቶ፣ ሕጉምብርዳ፣ በሪተኽላይና አበርገሌ ግንባሮች ወጥተዋል
የትግራይ ታጣቂዎች ከጦር ግንባሮች ለቀው መውጣት መጀመራቸው ተነግሯል።
ታጣቂዎቹ ለሰላም ስምምነቱ መከበር በሚል ከማይ ቅነጣል፣ ዛላምበሳ፣ ነበለት፣ ጨርጨር፣ ኩኩፍቶ፣ ሕጉምብርዳ፣ በሪተኽላይ እና አበርገሌ ግንባሮች ለቀው መውጣታቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
የኢፌዲሪ መንግስት እና ህወሓት ለቀናት ከወሰደ ድርድር በኋላ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሁለት ዓመቱን ጦርነት የሚያስቆም የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።
ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል ሰነድም በኬንያ ናይሮቢ ተፈራርመዋል።
የሁለቱ ወገኖች የጦር አዛዦችም የህወሃት ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱበትን ሁኔታ ተነጋግረው አቅጣጫ ማስቀመጣቸው አይዘነጋም።
በዚህ የሰላም ስምምነቱ ማስፍጸሚያ ሰነድ የህወሃት ታጣቂዎች ከጦር ግንባሮች ወደ ካምፕ ገብተው የተሃዶሶ ስራ ከተሰራ በኋላ ትጥቅ ፈተው ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉበት መርሃ ግብር ተቀምጧል።
ቴክኒካዊ ችግር ገጥሟል በሚል የትጥቅ ማስፈታት ሂደቱ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ባይሄድም የህወሃት ታጣቂዎች ከጦር ግንባሮች መውጣት መጀመራቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን በዛሬው እለት ዘግቧል።
ታጣቂዎቹ በአዛዦች ከተሰጣቸው ገለጻ (ኦሬንቴሽን) በኋላ ነው ግጭት ሊፈጥሩ ከሚችሉ የውግያ አካባቢዎች እንዲለቁ መደረግ የተጀመረው ብሏል ዘገባው።
የህወሃት ታጣቂዎች “ሰላም ከተፈጠረ፣ ውግያ የምንመርጥበት አንዳችም ምክንያት የለንም” ማለታቸውም ተገልጿል።
ህወሃት ታጣቂዎቹን ከጦር ግንባሮች ማስወጣት ስለመጀመሩ የኢፌዴሪ መንግስት እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።
ይሁን እንጂ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ የትግራይ ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱበትን ዝርዝር ዕቅድ የሚያዘጋጅ የባለሙያዎች የጋራ ኮሚቴ ከትናንት ህዳር 21 2015 ጀምሮ ስራ መጀመሩን አስታውቋል።
ኮሚቴው በሚያወጣው ዝርዝር እቅድ መሰረትም ትጥቅ የማስፈታት፣ ካምፕ የማስገባትና ተያያዥ ጉዳዮች ምላሽ ያገኛሉ ነው የተባለው።
የፕሪቶሪያው ስምምነት የህወሓት ትጥቅ መፍታት፣ ለተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች መጀመር፣ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ያሉ ሁሉንም የፌደራል ተቋማት መቆጣጠር፣ በትግራይ የተካሄደው ምርጫ እንዲሰረዝ እና ሌሎችም ነጥቦች ተካተውበታል።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት አካላት የተፈረመውን የዘላቂ ግጭት ማቆም ስምምነት ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን እየገለጹ ናቸው፡፡
ህወሓት ተዋጊዎቹን ከውጊያ ቀጣና እያራቀ መሆኑን በገለጸበት ወቅት ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
የፌደራል መንግስትም በቁጥጥሩ ስር ባሉ ቦታዎች የኃይል መሰረተ ልማት የመዘርጋት እና በህወሓት ቁጥጥር ስር ባሉ የትግራይ ክልል አካባዎች ጭምር የሰብአዊ እርዳታ እያደረሰ መሆኑን እና ይህም መንግስት ለስምምነቱ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብሏል።