በሰላም ንግግሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናቱን መንግስት ገለጸ
በመከላከያ በተያዙ አካባቢዎች ከማኅበረሰብ ጋር በመነጋገር ሕዝባዊ አስተዳደር የሚቋቋምበት መንገድ የተመቻቸ መሆኑ ተገልጿል
መንግስት “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁልፍ የሚባሉ የትግራይ ከተሞችን መቆጣጠሩን ቀጥሏል” ብሏል
በሰላም ንግግሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናቱን መንግስት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል የሚደረገው ድርድር በዛሬ እለት በደቡብ አፍሪካ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ መንግስት በአፍሪካ ኅብረት በኩል በደቡብ አፍሪካ በሚደረገው የሰላም ንግግር የሚሳተፍ መሆኑን አስታውቋል።
\አጋጣሚውንም የሰላም ንግግሩን ግጭቱን በሰላም ለመፍታት የሚቻልበት ዕድል አድርጎ እንደሚመለከትም አስታውቋል።
የሰላም ንግግሩ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መሥዋዕትነት እየተስተካከለ የመጣውን ሁኔታ የበለጠ ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር አድርጎ እንደሚወስደውም መግለጫው መላክቷል።
በሰላም ንግግሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ዛሬ ጠዋት ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራንም ነው መግለጫው ያመለካተው።
የህወሓት የተደራዳሪ ቡድን በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄደው ድርድር ላይ ለመሳተፍ ደቡብ አፍሪካ መድረሳቸውን የህወሓት አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።
ፕሮፌሰር ክንድያ ህወሓትን ወክለው ወደ ደቡብ አፍሪካ የተላኩት አባለት ማንነታቸውን ግልጽ አላደረጉም፡፡ ነገርግን ቀደም ሲል ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ስር ለመደራደር ፍቃደኛ መሆኑን በገለጸበት መግለጫው ቡድኑ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳን እና ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤን እንደሚያካትት መግለጹ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚስቴር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን የተደራዳሪውን ቡድን እንዲመሩ መሰየማቸውን መንግሰት ማስታወቁ ይታወሳል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው አክሎም “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁልፍ የሚባሉ የትግራይ ከተሞችን መቆጣጠሩን ቀጥሏል” ብሏል ።
“ይህንን ሲያደርግም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በከተሞች ውጊያ ሳይደረግ የህወሓትን ወታደራዊ ዐቅም ለማሽመድመድ የሚያስችል ስልት ተጠቅሟል” ነው ያለው መንግስት በመግለጫው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰብአዊ የእርዳታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ እየሠራ እንደሚገኝም መግለጫው አመላቷል።
የመከላከያ ሰራዊት በተቆጣተራው አካባቢዎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እንዲያፋጥኑ እየተደረገ መሆኑንም መንግስ አስታውቋል።
ከየአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመነጋገር ሕዝባዊ አስተዳደር የሚቋቋምበትንና ማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚጀምሩበትን መንገድ እያመቻቸ መሆኑንም ገልጿል።