በሰሜኑ ጦርነት አጥፊዎች የሚጠየቁበት እና ተጎጂዎች የሚካሱበት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ተዘጋጀ
በእርቅ ስም ከፍተኛ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ከተጠያቂነት ሊያመልጡ ይችላሉ የሚል ስጋት ይነሳል
መንግስት የሚካሄደው የሽግግር ፍትህ ሀገሪቱ ወደ ዘላቂ ሰላም የምትሸጋገርበት ምዕራፍ ነው ብሏል
የፌደራል መንግስቱንና ህወሓትን ወደ ሰላም በመራው የፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 10 መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ይደነግጋል።
ይዘጋጃል የተባለው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ተጠያቂነት ላይ ያነጣጠረ፣ እውነትን ማረጋገጥ፣ ለተጎጂዎች መፍትሄ መስጠትን ዓለማ አድርጎ ለእርቅና ለፈውስ ሲባል ይካሄዳል።
ለሁለት አመታት የዘለቀው ጦርነት በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ሶስት ክልሎችን ሰለባ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) እና አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት በጦርነቱ በተለያየ ጊዜ ባወጡት ሪፖርት አያሌ ሰዎች ተገድለዋል፤እስከ ጦር ወንጀል ሊደርሱ የሚችሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡
- የትግራይ ግጭት ተሳታፊዎች “በተለያየ መጠን” የሰብአዊ መብቶችን መጣሳቸውን የምርመራ ቡድኑ ገለፀ
- የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት በምን ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደረሱ?
በወርሃ ጥቅምት በተደረሰው ስምምነት የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማዕቀፍንና የሀገሪቱን ህገ-መንግስት መሰረት ያደረገ የሽግግር ፍትህ ለማድረግ ሁለቱ ወገኖች ስምም ላይ ደርሰዋል።
በዚህም መሰረት የመጀመሪያው የሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ፍትህ ሚንስቴር ለአል ዐይን አማርኛ ተናግሯል። በአሁኑ ሰዓት የሚወሰዱ እርምጃዎች እነዚህ ናቸው ብሎ መዘርዘር እንደማይችል የገለጸው ፍትህ ሚንስቴር፤ ፖሊሲው በባለሞያዎች ግብዓት ከዳበረ በኋላ ለህዝብ ይፋ ይሆናል ብሏል።
ፍትህ ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አወል ሱልጣን “መንግስት በቀጣይ በፍልስፍናው፣ ህግ ከማስፈን፣ ግለሰቦችን ከመጠየቅ፣ ተጠያቂነትን ማስፈንን በተመለከተ ከጸደቀ በኋላ ያሳውቋል” ብለዋል።
የሽግግር ፍትህ በኢትዮጵያ ያለው አረዳድና ተሞክሮ፣ ተጠያቂነት እስከምን ድረስ የሚለውና ሂደቱ ከጀርባው ያዘላቸው ስጋቶች አይን ተጥሎባቸዋል።
የሽግግር ፍትህ ምንትና ኢትዮጵያ
ሀገራት ከእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት ለመውጣት የሽግግር ፍትህን ቁልፍ መሳሪያ አድርገው ይጠቀማሉ። ይህ ስርዓት በመደበኛው የፍትህ ስርዓት የሚመራ ሳይሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የነበሩ ችግሮችን ቀርፎ ለቀጣይ አስተማሪ እርምጃዎች የሚወሰኑበትም ነው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ኃላፊ ያሬድ ኃ/ማሪያም የሽግግር ፍትህን ከፍትህ ጉድለቶች መሸጋገሪያ ድልድይ ማለት ነው ይላሉ።
“ፍትህ የሚለው ቃል ከጥሰት ጋር ሊያያዝ ይችላል። ሽግግር ደግሞ ከአንድ መጥፎ፣ ከፍተኛ ጥሰት ከነበረው ስርዓት ወደ ተሻለ ሰብዓዊ መብቶች ወደ ሚከበሩበት የሚያመራ ሀገርን ሚያሳልፍ መንገድ ነው። ስለዚህ መጥፎ አስቸጋሪ በነበረው ጊዜ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፤ የፍትህ መጓደሎች ፍትህ የሚያገኙበት መሸጋገሪያ ማለት ነው” ይላሉ።
ፍትህ ሚንስቴር በበኩሉ የበደል መቋጫ ማበጃ ስርዓትና መንግስት ቃል የሚገባበት ነው ይለዋል። የፍትህ ሚንስቴር የህዝብ ግንኘነት ኃላፊ አወል ሱልጣን “በአንድ ሀገር ሰላምና ብሄራዊ ደህንነት ከወደቀበት ስጋት ለመታደግ እንዲሁም በህዝቦች መካከል ግጭት ሲፈጠር ለመፍታት፣ ለደረሱ በደሎችና ጥሰቶች ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ለተጎጂዎች ካሳ ለመስጠትና ቁስልን አክሞ ለመሻጋር ሲባል የሽግግር ፍትህ ይካሄዳል” ብለዋል።
የስርዓቱ እርምጃ አስቸጋሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደነበር እውቅና ከመስጠት ይጀምራል። ከዛም የተፈጸሙት በደሎች በአግባቡ ተሰንደውና በበቂ ማስረጃ ተደግፈው፣ ተመርምረው መቀመጣቸውን መነሻ እንደሚያደርግ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድ ኃ/ማርያም ያነሳሉ። ፍትህና ተጠያቂነትን በውስጡ በመያዝም ምህረትንና ካሳንም አባሪ ያደረገ ነው ይላሉ።
ሆኖም ከሽግግር ፍትህ ጽንሰ-ሀሳብ ባሻገር የኢትዮጵያ ልምድ እምብዛምና የይስሙላ ስለመሆኑ ይነገራል። በተለይም ይህን ስርዓት ከእውነተኛ ፍትህ ይልቅ መንግስታት ሲለዋወጡ ቅቡልነታቸውን ለማሳደግና ለፖለቲካ ትርፋቸው መጠቀማቸው በትችት ይነሳል። በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት ያሬድ ኃ/ማርያም በጥቅሉ ኢትዮጰያ ውስጥ “ሽግግር” የሚለው ሀሳብ በተሳሳተ መንገድ ትርጉም ተሰጥቶታል፤ ከመንግስት ለውጥ ጋር ብቻ ይይያዛል ይላሉ።
ደርግ ከአጼ ኃ/ስላሴ መንግስት በትረ-ስልጣኑን ሲቆጣጠር፣ ኢህአዴግ ከደርግ ሲወስድ እንዲሁም በ2010ሩ “የኢህአዴግ ሽግሽግ” የተወሰዱ እርምጃዎች የሽግግር ፍትህና ኢትዮጵያ ላላቸው ግንኙነት ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው።
“በአብዮታዊ ለውጥ ሙሉ ለሙሉ የመንግስት ለውጥ ሲኖር ስልጣን የተቆጣጠረው መንግስት ቅቡልነቱን ለማሳደግ የሽግግር ፍትህን እንደ መሳሪያ ይጠቀምበታል። ለምሳሌ ኢህአዴግ ደርግን ሲጥል ወዲያውኑ የቀይ ሽብር ክስ ተመሰረተ። ወዲያው ባለስልጣናት መከሰስ ጀመሩ። ይህ ማለት ኢህአዴግ ራሱን የፍትህ ተቆርቋሪ፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ አርድጎ፤ ስልጣን ላይ የነበሩትን ደግሞ እስር ቤት በቁጥጥሩ ስር አድርጎ እንደ መሳሪያ ተጠቅሞበት ነበር። ዓላማውንም በተወሰነ ደረጃ እንዲስት ተደርጓል” በማለት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ስለ ኢትዮጵያ ልምድ ይገልጻሉ።
አቶ ያሬድ “የሽግግር ፍትህን አስቸጋሪ የሚያደርገው እንደ አሁኑ ያለንበት ለውጥ ነው። ምክንያቱም ስልጣን ላይ ያሉት መሪዎች እውነተኛ ሂደት ይደረግ ከተባለ በአንድም ይሁን በሌላ መንግድ ተጠያቂ ይሆናሉ። አጀንዳው ብዙ ጊዜ የሚገፋውም ለዚሁ ነው” ይላሉ።
መንግስት የሽግግር ፍትህ ትኩረት ካደረኩባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው ይላል። የፍትህ ሚንስቴር የህዝብ ግንኘነት ኃላፊ አወል ሱልጣን ለአል ዐይን አማርኛ ሲናገሩ ስርዓቱን ማስፈን ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ትልቅ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
“ሰዎች ሞተዋል፣ ንብረት ወድሟል፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽማል፣ አስገድዶ መድፈር ተፈጽሟል፣ ያለ ፍርድ ግድያም ብትይ ሁሉም ተፈጽሟል። የሽግግር ፍትህን በማስከበር ሂደት ውስጥ መንግስት በሚወስዳቸው እርምጃዎች የሀገሪቷን ሰላም ለማረጋገጥ፣ የሀገሪቷን መጻኢ እጣ ፈንታ ለመወሰን የራሱን ሚና ይጫወታል” በማለት አብራርተዋል።
በሽግግር ፍትህ ሊጠየቁ የሚችሉ ተዋንያኑ እነማን ናቸው?
ሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ለተፈጸሙ ወንጀሎችና ጥሰቶች “ተጠያቂ” የተባሉ ተዋንያን ስም እዚህም እዚያም ሲነሳ ነበር። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰማኮ)፣ የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎችም ድርጅቶች (ሙሉ የጦርነት ቀጣናውን ባይሸፍንም እንኳ) ባደረጓቸው ምርመራዎች ከፍተኛ የሆነ የጦር ወንጀል፣ በሰው ስብዕና ላይ ያነጣጠረ ወንጀልና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ድርጅቶቹ በሪፖርታቸውም ተጠያቂ ያሉት ሁሉንም አካላት ነው። ከመንግስት ታጣቂዎች ጀምሮ መከላከያ ሰራዊትን፣ የኤርትራ ጦር፣ የህውሓት ሰራዊትና የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ለተፈጸሙ ጥሰቶች ተጠያቂ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ኃላፊ ያሬድ ኃ/ማሪያም ሁሉም ጥሰት የፈጸሙ ተዋንያኖች በዚህ የሽግግር ፍትህ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ይላሉ። በዝርዝር እነማን ናቸው የሚጠየቁት የሚለው የህግ ባለሞያዎች፣ የፍ/ቤትና ዐቃቢ ህግ ስራ መሆኑን የሚያነሱት ኃላፊው፤ “ሁሉም እንደየ ተሳትፏቸው መጠን ተጠያቂ ይሆናሉ” ብለዋል። ከተሳትፎ መጠን ባለፈ “የበደሉ አይነት” እንደሚወስነው በማንሳት።
በሰሜኑ ጦርነት ላይ ምርመራ ያደረጉ ተቋማት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን (ኢሰማኮ) ጨምሮ ኤርትራ ወታደሮች የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል። በሽግግር ስርዓቱ እንደ ኤርትራ ጦር ያሉ የውጭ ኃይሎች የሚጠየቁበት የህግ አግባብ ስለመኖሩ የጠየቅናቸው አቶ ያሬድ ፤ የለም በለዋል። ምን አልባትም በዓለም አቀፍ ፍ/ቤት ካልተጠየቁ በቀር የሀገሪቱንም ሁኔታ እንዴት ገባ የሚለው ነገር ያወሳስበዋል ብለዋል።
ንብረታቸው ለወደመባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በጦርነቱ ቀጥተኛ ጉዳት ተደረሰባቸው ሰዎች ካሳ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። “የንብረት ካሳና መልሶ የማቋቋም፣ የስነ-ልቦና ጉዳት፣ የጤና ጉዳት ለደረሰባቸው በቂ የክህምና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል።
በሽግግር ፍትህ ላይ የሚኖረው ስጋት
ለሰሜኑ ጦርነት የሽግግር ፍትህን ይሰፍናል ሲባል የተጠያቂነት ጉዳይ ትልቁን ስፍራ ይይዛል። የሀገሪቱን ልምድና የፖለቲካ ባህል በመመስረት ምን ያህል እውነተኛ ተጠያቂነት ይኖራል ሲሉ የሚጠይቁ አያሌዎች ናቸው።
በእርቅ ስም ከፍተኛ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ከተጠያቂነት ሊያመልጡ ይችላሉ የሚል ስጋት ይነሳል፡፡
ያሬድ ኃ/ማርያም በሂደቱ ስጋታቸው ትናንሽ ወንጀለኞችን ለማሳያ ነካክቶ ማለፍ እንደሆነ ይናገራሉ። የሽግግር ፍትህ የሚጠይቀው የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለ የሚሉት ያሬድ፤ በተሰራው ወንጀል ልክ መጠየቅን የሚያምን የፖለቲካ እርምጃ መኖር እንደለበት ያሰምራሉ።
“የይስሙላ ከሆነ ግን ጥቂት ሰዎችን ወደ ፊት በማምጣት፤ ከፍተኛ ወንጀል የሰሩትን በሰላም ስምምነት፣ በእርቅ እጃቸው በደም እንደጨቀየ ሳይነኩ ያልፋሉ” ይላሉ። በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ከግጭት በኋላ ሰላም የማይመጣው ለዚህ ነው የሚሉት የሰብዓዊ መብት ተማጋቹ፤ ይህም ማስመሰያና መበቀያ እንጂ እውነተኛ ፍትህ አይደለም ባይ ናቸው።
“ለምሳሌ ጎንደር ውስጥ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ወሎ ውስጥ በሴቶች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። ተጎጂዎች የወታደሮቹን ቁጥር እንጂ ማንነት [ስም] ሊናገሩ አይችሉም። ‘ይህን አይነት መለያ የለበሱ ወታደሮች ደፍረውኛል’ ነው ሊሉ የሚችሉት። ወታደሮቹ አንድ ቦታ ላይ የሚቀመጡ አይደሉም። ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። ሁለተኛ ነገር በግጭቱ ህይወታቸው ሊያልፍ ይችላል። ጥፋቱ በተፈጸመበት ቦታና ወቅት እዛ አካባቢ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ጦር ሲመራ የነበረው ማን ነው? ስለዚህ በዚህ አካሄድ ከሄድን እስከ ጀነራሎች ድረስ ተጠያቂ ይሆናሉ። ምን አደረጉ? ለመከላከል ምን ሰሩ? አስቁመዋል ወይ? የሚለው ይጠየቃል” በማለት የእውነተኛ የሽግግር ፍትህ ተጠያቂነት እስከ ላይ ድረስ መሆኑን ይገልጻሉ።
ያሬድ ኃ/ማርያም ተጠያቂነት እስከ ላይ ድረስ የሚፈቅድ የፖለቲካ ምህዳር የለም በሚል በዚህ ረገድ ተስፈኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል። መንግስት ግን ፖሊሲው ትናንሽ አሳዎች ላይ ብቻ አያነጣጥርም ብሏል። የፍትህ ሚንስቴር የህዝብ ግንኘነት ኃላፊው አወል ሱልጣን የሀገሪቱ ሁኔታ አባጣ ጎርባጣ መሆን ሂደቱን አልጋ በአልጋ እንደማያደርገው አስቀድመን ተረድተናል ያሉ ሲሆን፤ “ይሳካልናል” በሚል ግን ትልቅ ተስፋ ተሰንቋል ብለዋል።
መንግስት “በጥርጣሬ ከማየት ይልቅ ደግፉኝ። ስኬቱነቱን የጋራ ጉዳይ አድርጎ መመልከት ያሰስፈልጋል” ብሏል።
“የሚያነጣጥረው አነስተኛ ወንጀል የፈጸሙት፣ ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መርሀ-ግብር አይደለም። የትኛውን የማህበረሰብ ክፍል የማይለይ፣ በእኩል መጠየቅ የሚያስችል ስርዓትን የሚዘረጋ ነው። ትናንሾቹ ላይ ማተኮር የማያዛልቅ ነው። አንደኛ ማህበረሰቡ እንዲያምነን እንፈልጋለን። ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ መተማመን እንዲኖረው እንፈልጋለን። በአጠቃላይ በመንግስትና በስርዓቱ ላይም ይህን ማዳበር የሚቻለው ተጨባጭ ተጠያቂነትና እኩልነት ሲኖር ነው። ይህን ከግምት ውስጥ ያስገባ ስራ ነው እየተሰራ ያለው” ብለዋል አወል ሱልጣን።
ለእውነተኛ የሽግግር ፍትህ ምን ይደረግ?
ለሽግግር ፍትህ የመጀመሪያ እርምጃ ግልጽ ምስል የሚሰጥ የተጠናከረ ምርመራ መሆኑን ባለሞያዎች ያነሳሉ። በመጀመሪያ “ገለልተኛ” በሆነ አካል የደረሰው የጉዳት መጠን መታወቅ አለበት የሚሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድ ኃ/ማርያም፤ ለጉዳቱ መከሰት ተጠያቂ የሆኑ ከፖለቲካ መሪዎች እስከ ጦር አዛዦች ድረስ አንድ ሁለት እየተባሉ መለየት አለባቸው ይላሉ።
“የትኛው ክፍል፣ ከማን ትዕዛዝ ተቀብሎ ነው ይህን ያደረገው? ባደረሰው ጥቃትስ እነማን ላይ ምን ጉዳት ደረሰ የሚለው በህውሓት በኩል ያሉ፣ በፌደራል መንግስቱ በኩል ያሉ የመንግስት ሹሞችና ታጣቂዎች እያለ በሁሉም ዙሪያ የደረሰው ጉዳትና መጠን ተለይቶ በባለሞያ መቀመጥ አለበት” ይላሉ።
በሰሜኑ ጦርነት የደረሱ ጥሰቶችንና ውድመቶችን በሚመለከት በመንግስት የተቋቋመው የሚንስትሮች ግብረ-ሀይል ሲመመረምር እንደነበር ይታወሳል።
ተሟጋቹ ሁለተኛ እርምጃው በጎ ትብብርና በጎ ፈቃድ ነው ይላሉ። ገለልተኛ ምርመራ ለማድረግም ሆነ አጥፊዎችን ለመለየት፣ ተጠያቂ ለማድረግ የመንግስትና በጥሰቱ የተሳተፉ ኃይሎች ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል። ይህ የሚያስፈልገው ስርዓቱ ከወንጀል ፍትህ የተለየ መሆኑ ነው። “በወንጀል ቢሆን የተሳተፉ አካላት ተባበሩም አልተባበሩም ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም። ነገር ግን ዛሬ ባለው አውድ አጥፊ የመንግስት ባለስልጣናት እጃቸው ኖሮበት ፍ/ቤት ማቅረብ የግድ የመንግስትን ፈቃደኝነት ይጠይቃል።”
በደሎችንና ወንጀሎችን በስምምነትና በእርቅ ስም ጨፍልቆ ከተሄደ እዳው ገብስ ይሆናልም ብለዋል። “ከሳሽ፣ ነጻ ፍ/ቤት፣ ነጻ ከባቢ እስኪመጣ ድረስ ይቆያል ማለት ነው። ስለዚህ የፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነት ይፈልጋል።”
ፍትህ ሚንስቴር በጉዳዩ ላይ ዘርዘር ያለ ማብራሪ መስጠት እንደማይችል ገልጾ፤ የሽግግር ፍትህ ግን የመንግስት ዋነኛ ከሚላቸው ሦስት አጀንዳዎች ውስጥ ይመደባል ብሏል። ለስርዓቱ መሳካት ከሁሉም አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግም ተናግሯል።
አል ዐይን አማርኛ ስርዓቱ የትኛውን ምርመራ መሰረት አድርጎ ይካሄዳል ሲል የጠየቃቸው የፍትህ ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከመጥቀስ ተቆጥበዋል። የፖሊሲውን ዝርዝር አፈጻጸምና መርሀ-ግብር እንዳለቀ እናሳውቃለን ብለዋል።