መንግስት የሰላም ሂደቱ በአፍሪካ ህብረት መሪነትና አስተባባሪነት እንዲከናወን አቋም ይዟል
ከህወሓት ጋር የሚደራደረውና ከወር በፊት የተዋቀረው “ሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ” ስራ መጀመሩን አስታውቋል።
የኮሚቴው አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድን ሁሴን በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተቋቋመው አብይ ኮሚቴ ስራ ጀምሯል ብለዋል።
ኮሚቴው የመጀመሪያ ስብሰባውን ማካሄዱንም ሬድዋን ሁሴን ጠቅሰዋል።
ኮሚቴው በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለሚካሄደው የሰላም ውይይት የራሱን የአሰራርና ሥነምግባር አካሄድ ተወያይቶ መወሰኑንም አምባሳደር ሬድዋን ጠቁመዋል፡፡
ኮሚቴው በስሩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በመደራጃትም ኃላፊነት ተከፋፍሎ ስራውን መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር የሰላም አማራጮች እንዲታዩ እና የፌደራል መንግስቱን ወክለው በሰላም ውይይቱ ላይ የሚሳተፉ አባላት መመደባቸው ይታወሳል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ቡድኑ ሰባት አባላትን በውስጡ የያዘ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከወር በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበረቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል ኮሚቴ መቋቋሙን መግለፃቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽ፤ ከህወሓት ጋር ለመደራደር ኮሚቴ ተቋቁሞ አስፈላጊ ሁኔታዎችን እየተያደረጉ ነውም ብለዋል።
ህወሓት በበኩሉ በኬንያ መንግስት በተጠራው ድርድር የሚሳተፍ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን በሊቀ መንበሩ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ማስታወቁ ይታወሳል።