መንግስት የኢትዮጵያን ስም የሚያጠፉ ምእራባውያንን እንደማይታገስ አስታወቀ
መንግስት እና በህወሓት መካከል ሰኞ የተጀመረው ድርድር ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል
መንግስት የፖለቲካ አላማ ያለው ክስ ከሚያቀርቡ መንግስታት እና አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጤን መገደዱም አስታወቋል
የኢትዮጲያ መንግስት ምእራባውያን አካላት በኢትዮጲያ መንግስት ላይ የሚያደርሱትን በሀሰት ሰም የማጥፋት ዘመቻ እንደማይታገስ አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ምእራባውያን አካላት "በኢትዮጲያ በጣም ዘግናኝ ሆነ ወንጀል ሊፈጸም ይችላል" የሚለውን የህወሓት ፕሮፓጋንዳ ማስተጋባታቸው ነውር ነው ሲል ገልጿል።
የኢትዮጲያን ሰም እያጠፉ ያሉት የተወሰኑት በመታለል መሆኑንን የገለጸው መንግስት የተወሰኑት የውሸት ክስ በማቅረብ ኢትዮጲያ እጅ እንድሰጥና እና ህወሓት እንዲድን ለማድረግ ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ ትእዛዛቸውን ያልተቀበለቻቸው አንዳንድ የምእራባውያን ባለስልጣናት ስም የማጥፋቱን ዘመቻ በግልጽ እያራመዱ መሆናቸውን መንግስት ገልጿል።
በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው የሰም ማጥፋቱና ሀሰተኛ ክስ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ እንደማይቀይረው የገለጸው መንግስት ለፖለቲካ አላማ በጣም ከባድ ወንጀል እየተፈጸመ ነው የሚል ክስ የሚያቀርቡት ኃላፊት የጎደላቸው ናቸው ብሏል።
መንግስት ያልተረጋገጠ እና የፖለቲካ አላማ ያለው ክስ ከሚያቀርቡ መንግስታት እና አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጤን መገደዱም አስታወቋል።
በመንግስት እና በህወሓት መካከል በድጋሚ በነሀሴ ወር የተቀሰቀሰው ጦርነት የቀጠለ ሲሆን መንግስት "ቀልፋ የሚባሉ የትግራይ ከተሞችን" መቆጣጠሩን ማስታወቁ ይታወሳል። ህወሓት አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እንደሚፈልግ እየገለጸ ነው።
ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት በደቡብ አፍሪካ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ድርድር እየተካሄደ ነው። ባለፈው ሰኞ የተጀመረው ድርድር ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄደው ድርድር አሜሪካ፣ተመድ እና ኢጋድ በታዛቢነት መሰየማቸውን ህብረቱ ማስታወቁ ይታወሳል።