የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያና ሶማሊያ ጉዳይ ላይ ሊመክር ነው
ሶማሊያ ኢትዮጵያ የተመድን ቻርተር ጥሳለች በሚል ምክር ቤቱ ስብሰባ እንዲቀመጥ አመልክታ ነበር
የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባውን የጠራችው ፈረንሳይ ነች
የተባበሩት መንግስታ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያና ሶማሊያ ጉዳይ ላይ ሊሰበሰብ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱን ተከትሎም ሶማሊላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትለው ሶማሊያ የዲፕሎማሲ የበላይነት ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በዚሁ መሰረት ሶማሊያ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት የተመድን ቻርተር ጥሷል በሚል ምክር ቤቱ ስብሰባ እንዲቀመጥ አመልክታ ነበር።
ይህንን ተከትሎም የጸጥታው ምክር ቤት የወሩ ፕሬዝዳንት ፈረንሳይ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ጉዳይ ላይ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት አጀንዳ ስር ለመምከር ስብሰባ መጥራቷ ታውቋል።
የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው እለት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ባለው ችግር ዙሪያ በዝግ እንደሚመክርም ነው ከተመድ የተገኘው መረጃ የሚያመልከተው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ሀና ስርዌ ቴተ በጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባው ላይ ቀርበው በኢትዮጵያና ሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሏል።
የጥር ወር የጸጥታው ምር ቤት ፕሬዝዳንት ፈረንሳይ ስብሰባውን የጠራችው ሶማሊያ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል በተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ በስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ በሰጡት ማብራሪያ፤ “የቀይ ባህርን የመጠቀም ጥያቄያችን ህጋዊ መሆኑን ለዓለም አሳይተናል፤ የእኛ ፍላጎት ቀይ ባህርን መጠቀም ብቻ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
“በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግስታት መካከል ችግር ይፈጠራል ብዬ ስለማላስብ፤ በህዝቦች መካከል ጥላቻና ቁርሾ እንዳይፈጠር በሰለጠነ እና በተረጋጋ መንገድ መምራት ይፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ከሰሞኑ ከአልጄዚራ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ጉዳዩን ሁላችንንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ መፍታት ይቻላል ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ወደብ ቢኖራት ተቃውሞ የለንም፣ ለድርድርም ዝግጁ ነን ነገር ግን የሌላ ሀገር ግዛትን በመውሰድ ግን ሊሆን አይገባም" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።