በጋሸና ግንባር ዐርቢት፣ አቀት፣ ባዶና ጋሸና ከተማ ነፃ መውጣታቸውን አስታውቋል
በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እየተመራ ወደ ከፍተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የገባው የኢትዮጵያ ሰራዊት “ድል እያስመዘገበ” መሆኑን መንግስት እየተመራ ወደ ከፍተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የገባው የኢትዮጵያ ሰራዊት “ድል እያስመዘገበ” መሆኑን መንግስት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽ አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ “በተለያዩ ግንባሮች በርካታ ድሎች እየተመዘገቡ ነው” ብለዋል።
“በዚህም ጋሸና ግንባር ዐርቢት፣ አቀት፣ ዳቦና ጋሸና ከተሞች ነፃ ወጥተዋል” ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ በዚህ ግንባር ህወሓት የአካባቢውን ህብረተሰብ በማስገደድ የገነባው ባለ ብዙ እርከን መሰበሩንም አስታውቀዋል።
በርካታ የነፍስ ወከፍ፣ የብድን እና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች መማረኩንም ያነሱት ሚኒስትሩ፤ “ህወሓት ታጣቂዎች ራሳቸውን እና የዘረፉትን ንብረት ይዘው የሚወጡበትን እድል መሉ በሙሉ ተዘግቶባቸዋል” ሲሉም አስታውቀዋል።
ዶ/ር ለገሰ በመግለጫቸው አክለውም፤ “በጋሸና ግንባር ላይ የተገኘው ድል በላሊበላ፣ ወልዲያ፣ ሰቆጣ እና ደሴ አካባቢዎች ህወሓት የተቆጣጠራቸውን ስፍራዎችን በቀላሉ ነፃ ለማውጣት ያስችላል” ሲሉም ተናግረዋል።
“ጋሸናን የተቆጣጠረው የወገን ጦር በአሁኑ ሰዓት ወደ ወልዲያ፣ ላሊበላ እና ወገል ጤና አቅጣጫ እየገሰገሰ ይገኛል” ሲሉም አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ በወረ ኢሉ ግንባር፤ “ወረ ኢሉ፣ ገነቴ፣ ፊንጮፍቱ እና አቀስታ ከተሞች ከህወሓት ታጣቂዎች ሙሉ በሙሉ ነፃ በመውጣት በወገን ኃይል እጅ ይገኛሉ” ሲሉም ተናግረዋል።
ሸዋ ግንባርም መዘዞ፣ ሞላሌ እና ሸዋ ሮቢት መውጣታቸውንም ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
ምስራቅ ግንባርም ቀደም ሲል ነፃ ወጣ የወጡት ካሳ ጊታ፣ ዋኢማ፣ ጭፍራ ና ሌሎችም ከተሞች ሙሉ በሙሉ ፀድተው የአካባቢው አስተዳደር ወደ ቦታው በመመለስ አካባቢውን መልሶ የማደራጀት ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር የተፈረጀው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ጥቃት መክፈቱንና ይህንም ለመቀልበስ እንደሚንቀሳቀስ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግስት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄ የሚገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ከግንባር ሆነው ባስተላለፉት መልእክት፤ ጦርነቱን መንግስት ማሸነፉ የማይቀር ስለሆነ የህወሓት ታጣቂዎች እጃቸውን ለጸጥታ አካላት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።