“ሠራዊቱ የምዕራፍ አንዱን ጦርነት አጠናቅቆ ለቀጣይ ግዳጅ እየተዘጋጀ ነው”-ጄ/ል አበባው ታደሰ
ህወሓት አሁንም ትንኮሳውን እንዳላቆመም ነው የተናገሩት
ከህወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት አለመጠናቀቁንም ጄነራሉ ገልጸዋል
የሃገር መከላከያ ሰራዊት ለቀጣይ ግዳጅ እየተዘጋጀ መሆኑን የሰራዊቱ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ ገለጹ።
ጄ/ል አበባው ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ሠራዊቱ የምዕራፍ አንዱን ጦርነት አጠናቅቆ ለቀጣይ ግዳጅ እየተዘጋጀ ነው” ብለዋል፡፡
ሰራዊቱ ከህወሓት ያነሰ የሰው ኃይል ቁጥር እና ትጥቅ ይዞ ወደ ጦርነት መግባቱን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ “የሰራዊቱ ስንቅ ኢትዮጵያዊነት” ነበር ብለዋል።
ሠራዊቱ ጦርነቱ ሲጀመር ከ44 ሺህ ባልበለጠ የሰው ኃይል ከ250 ሺህ የሚልቀውን የህወሓትን ኃይል ከነተጨማሪ ጀሌዎቹ መግጠሙንም ጄነራሉ ተናግረዋል።
በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት ገና አልተጠናቀቀም ያሉት ጄነራል አበባው ሠራዊቱ የምዕራፍ አንዱን ጦርነት አጠናቅቆ ለቀጣይ ግዳጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል፤ ቡድኑ አሁንም ትንኮሳውን እንዳላቋረጠ በመጠቆም።
ህወሓትን ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች በማስወጣት የተገኘው ድል “ህዝባዊ ነው” ያሉት ጄነራሉ የጠላትን የማድረግ አቅም ያዳከመ እና ከፍተኛ የሰው ኃይል እና የንብረት ኪሳራ ያደረሰ መሆኑንም ገልፀዋል።
በጋሸና፣ ሚሌ እና በመሀል ግንባሮች ፈታኝ ውጊያዎች መደረጋቸውን የገለፁት ጄነራሉ ሠራዊቱ ከፍተኛ ጀብዱ የሰራባቸው እንደነበሩም ተናግረዋል።
ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ የወሰደው ቁርጠኝነት የሠራዊቱን ዝግጁነት አቅም ያሳደገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሰራዊቱ የጦርነቱን የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠናቀቁን ተከትሎ ነጻ ባወጣቸው የምስራቅ አማራ የአፋር አካባቢዎች ጸንቶ እንዲቆይ መታዘዙ ይታወሳል፡፡
ከአሁን ቀደም ካጋጠሙ ችግሮች ልምድ በመቅሰም የተሰጠ ነው በተባለው በዚህ ትዕዛዝ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱና ቅሬታዎችም ሲቀርቡ ነበር፡፡
ከህወሓት ጦር ነጻ ያልወጡ አካባቢዎች እንዳሉ በመግለጽ የውሳኔውን አግባብነት ያጠየቁ አካላትም ነበሩ፡፡
ጄ/ል አበባው ሰራዊቱ የሚለካው በስራው ስኬት እና በግዳጅ አፈፃፀሙ እንጂ በብሄሩ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት በነበረው የብሄር ተኮር የሠራዊት ግንባታ ዋጋ የከፈለው እራሱ ሠራዊቱ ነው ያሉት ጄነራል አበባው ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ እና በሞያው ብቁ የሆነ ሠራዊት እየተገነባ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
በቅርቡ የተካሄደው ወታደራዊ የማዕረግ እና የሜዳልያ ሽልማት በግዳጅ አፈፃፀም ላይ የተመሰረተ፣ በየደረጃው ላሉ እዞች ማዕረግ የተሰጠበት፣ የሠራዊቱ አመራሮችን የሚመጥን እና የሠራዊቱን ሞራል የገነባ ነበርም ብለዋል።
ጄነራል አበባው ታደሰ በቅርቡ የማዕረግ ሹመት ካገኙ የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች መካከል መሆናቸው ይታወቃል፡፡