በተመድ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ስብሰባ ላይ ድምጸ ተዓቅቦ ካደረጉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ውይይት መጀመሩን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገለጸ
በቀጣይ በሚደረገው በብሄራዊ ውይይት ህወሓትን እንደማይመለከትም ተገልጿል
አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ኢትዮጵያ ግፊት ማድረጓን ትቀጥላለች ተብሏል
በተመድ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ስብሰባ ላይ ድምጸ ተዓቅቦ ካደረጉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ውይይት መጀመሩን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ባሳለፍነው ሳምንት በተመድ የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ተፈጽመዋል ባላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ አዲስ ምርመራ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።
በዚህ ጉባኤ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ በተደረገው ምርጫ ላይ የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት በውሳኔው ላይ ድምጸ ተዓቅቦ ማድረጋቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ምን አደረገ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር ዲና ከሀገራቱ ጋር ውይይት አድርገናል ብለዋል።
"ጉዳዩ ለፖለቲካ ፍላጎት ሲባል የተደረገ ነው፣ ምዕራባውያን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳስቧቸው አይደለም ጉዳዩ የቅኝ ግዛት ሀሳብ ነው" በሚል ድምጽ ተዓቅቦ ካደረጉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር በዲፕሎማሲ መንገድ ተነጋግረናል ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋ።
ሱዳን፣ ማላዊ፣ ቶጎ፣ ሴኔጋል፣ ሊቢያ እና ሞሪታኒያ በተመድ የሰብዓዊ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በተሰጠው ድምጽ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል በድምጸ ተዓቅቦ የወጡ አገራ ናቸው።
አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እንዲኖራት ኢትዮጵያ ግፊት ማድረጓን እንደምትቀጥልም አምባሳደር ዲና ተናግረዋ ።
አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት በሚል ጥያቄው አሁን ላይ ሲነሳ የመጀመሪያ አይደለም ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ጥያቄው የረጅም ጊዜ ነው ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ከአፍሪካ ውጪ ያሉ አህጉራት እና ሀገራት ድጋሚ በመነሳት ላይ ነውም ብለዋል።
በቀጣይ የሚደረገው ብሄራዊ ውይይት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሀትን እንደማይመለከትም አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
ይህ ውይይት የተዘጋጀው ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ወደ ግጭት እና ጦርነት የሚያስገባት ምንድን ነው? በሚለው አጅንዳ ላይ በዋነኝነት ለመወያየት የተዘጋጀ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
እነማን ይሳተፋሉ፣ አጅነዳዎቹ እንዴት ይቀረጻሉ ፣አሁን ላይ እና ወደ ፊት ለሀገራዊ ግንባታ ስራዎቻችን ሊያጋጥሙን የሚችሉ ችግሮች ምንድን ናቸው እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ተሳታፊዎቹ ይወያያሉም ብለዋል።
ይሁንና ለችግሮቻችን ዘላቂ እና አካታች መፍትሄዎችን ለመቅረጽ የግድ ተቋም ስለሚያስፈልግ ይሄንን የሚመራ የፌደራል ተቋም በመቋቋም ላይ መሆኑንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።