መንግስት “ሰላም ፈላጊ” የህወሓት አባላትን ያካተተ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገለፀ
መንግስት በትግራይ መሰረተ ልማት ለማሟላት በሚያደገው ጥረት ህወሓት እንቅፋት እንደሆነበት ገልጿል
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጃ በኋላ የትግራይ ልዩ ሃይል በኮረም በኩል ተኩስ መክፈቱን ገልጿል
መንግስት የትግራይን ቀውስ ለመፍታ ሰላማዊ መንገድን የሚመርጡ የህወሓት አባላትን ጨምሮ ሁሉንም ያካተተ ውይይት ለማድረግ መዘጋጀቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ደመቀ በዚህ ጊዜ እንዳሉት መንግስት በትግራይ ያለውን ቀውስ ለመፍታት ህጋዊ ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ሰላማዊ መንገድን ከመረጡ የህወሓት አባላት፣ የግል ባለሀብቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ባለደርሻ አካላት ጋር አካታች ውይይት ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
የፌደራል መንግስት በትግራይ የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ ለጊዜው የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉንም ተናግረዋል።
መንግስት የተናጠል ተኩስ ቢያውጅም የትግራይ ልዩ ሀይል በኮረም በኩል ተኩስ መክፈቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የባንክ አገልግሎት መልሶ ማስጀመርን በሚመለከት ባንኮችን አስገድዶ ስራ ጀምሩ ማለት እንደማይችል መንግስት አስታወቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው ይህንን ያሉት።
ሚኒስትር ዴኤታው መንግስት ያወጀው የተናጠል ተኩስ አቁሙ እርምጃን ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ እንዳደነቀው ገልጸው የባንክ፣ የመብራትና የስልክ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ህወሓት እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል።
ባንኮች በሚመለከት ለትርፍ ስለሚሰሩ፤ ዋስትና ካልተገባላቸው ለመስራት እንደሚቸገሩ ያኑሰት አምባሳደር ሬድዋን፤ መንግስት ግን ባንኮችን አስገድዶ ባንኮችን አግልገሎት ጀምሩ ማለት እንደማይችል አንስተዋል።
ህወሓት የመብራትና የስልክ አገልግሎት መስመሮችን ቆርጦ እንደነበር የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን እነዚህን መሰረተ ልማቶች መንግስት ጠግኖ ወደ አገልግሎት መልሶ እንደነበር ገልጸዋል።
ህወሃት የመብራትና የስልክ አገልግሎት መስመሮችን ለመጠገን ወደ ትግራይ የሄዱ መሃንድሶችን መግደሉንም ገልጸዋል።
በመሆኑም ህወሓት ይህንን የግድያ ወንጀል እየቀጠለ ባለበት በዚህ ሁኔታ የመብራትና የስልክ አገልግሎት ወደ ስራ ለማስገባት የፌዴራል መንግስት እንደሚቸገር አንስተዋል።
የፌደራል መንግስት በትግራይ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ያሳለፈው አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ተፈላጊዎች ለመያዝ ተብሎ ብዙ ነገር ዋጋ ላለመክፈል መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ሬድዋን፤ የተኩስ አቁም እርምጃው ነገሩን ሰከን ብሎ ለማየትና ሌላ አማራጭ ለመመልከት እንደሆነም አንስተዋል።
የፌደራል መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያደርግም ህወሓት ግን አሁንም ግጭት እያስነሳ መሆኑን ጠቅሰዋል።በተለይም በኮረም በኩል የትግራይ ልዩ ሀይል ተኩስ ከፍቶ እንደነበርም አንስተዋል።
አሁን ላይ የሰብአዊ መብት ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች መጥተው ማገዝ የሚፈልጉ አካላት ይህንን እንዲያደርጉ ቀለል ያለ ቪዛም እንደሚዘጋጅላቸው አንስተዋል።
የእርዳታ አውሮፕላኖችም አዲስ አበባ ሲያርፉና ሲነሱ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውና ከፍተሻ በኋላ መሄድ እንደሚችሉ አንስተዋል።