የትግራይ ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊት እያደረገ ላለው ትብብር መንግስት ምስጋና አቀረበ
የትግራይ ሕዝብ የህወሕትን የምስለኔ ቴአትር ትቶ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር የጀመረውን ትብብር እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርቧል
በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ያለው ድርድር እንደቀጠለ ነው
"የትግራይ ሕዝብ የህወሕትን የምስለኔ ቴአትር ትቶ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር የጀመረውን ትብብር ሊያጠናክር ይገባል" ሲል መንግስት ጥሪ አቀረበ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ "መከላከያ ሰራዊቱ መሥዋዕትነት የታሰበውን ግብ እንዲያሳካ የትግራይ ሕዝብ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል" ብሏል።
"የመከላከያ ሠራዊቱን በመንከባከብ፣ ስንቅ በማቀበል፣ ስለተደበቁ ጀሌዎችና የጦር መሣሪያዎች መረጃ በመስጠት፣ መንገድ በመምራት እና አካባቢውን በመጠበቅ የትግራይ ሕዝብ ከሠራዊቱ ጋር ተሰልፏል" ያለው መንግሥት ለዚህም ምስጋና አቅርቧል።
"የትግራይ ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ያለው ቅንጅት ሕወሐትን አስደንግጦታል" ያለው መግለጫው፣ በዚህም የተነሣ "ምስለኔዎች ሊያስተዳድሩህ እየመጡ ነው" የሚል ውዥንብር እየነዛ ነው" ብሏል።
"የትግራይ ሕዝብ በራሱ ልጆች እንጂ በማንም ሊተዳደር አይገባም" ያለው መንግስት፣ ፌዴራላዊ ሥርዓቱም ይሄንን አይፈቅድም፣ ሕወሐትም ይሄንን ያውቃል" ሲል አስታውቀዋል።
"በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ የህወሓትን የምስለኔ ቴአትር፣ በምስለኔነት ለኖረው ለሕወሐት ትቶ፣ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር የጀመረውን ትብብር እንዲያጠናክር መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።
በመንግስት እና በህወሓት መካከል በድጋሚ በነሀሴ ወር የተቀሰቀሰው ጦርነት የቀጠለ ሲሆን መንግስት "ቀልፋ የሚባሉ የትግራይ ከተሞችን" መቆጣጠሩን ማስታወቁ ይታወሳል። ህወሓት አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እንደሚፈልግ እየገለጸ ነው።
ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት በደቡብ አፍሪካ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ድርድር እየተካሄደ ነው። ባለፈው ሰኞ የተጀመረው ድርድር እንደቀጠለ ነው
።በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄደው ድርድር አሜሪካ፣ተመድ እና ኢጋድ በታዛቢነት መሰየማቸውን ህብረቱ ማስታወቁ ይታወሳል።