“ለሰላም የዘረጋነው እጅ ምንም ዋጋ ስላላገኘ ጦር እንዲይዝ እየተገደደ ነው”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላፈዋል
ጠ/ሚ ዐቢይ “ኢትዮጵያ በዓመቱ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚገባ አስጠብቃ ችግሯን ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ትታገላለች” ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ “ለሰላም የዘረጋነው እጅ ምንም ዋጋ ስላላገኘ ጦር እንዲይዝ እየተገደደ ነው” አሉ።
ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ በነገው እለት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የመስቀል በዓል አስመልከቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም “የመስቀል በዓል ያለፈውን ፈተና የምናስወግድበትና ለመጪው ተስፋ የምንሰንቅበት ነው” ብለዋል።
“የአከባበሩ ሥነ ሥርዓትና የሽማግሌዎች ምርቃት ይሄንን ያሳየናል፤ ኢትዮጵያም በዚህ ዓመት የከረሙ ችግሮቿን እንድትፈታና ገበታዋን ለልጆቿ በሚያስፈልጋቸው ምግብ እንድትሞላ፣ ኢትዮጵያን የምንወድ ሁሉ ቆርጠን እንድንነሣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አክለውም ስለ ሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያነሱ ሲሆን፤ “ትእግሥታችን እንደ ፍርሃት፣ ሰላም ፈላጊነታችን እንደ ድክመት ተቆጥሮ ሦስተኛ ዙር ጥቃት ተፈጸመብን” ብለዋል።
“በዚህ የተነሣ ሀገራዊ ሕልውናችንን ለማስጠበቅ ስንል ወደ መከላከል እንድንገባ ተገደናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያን ከመጥፋት ለመታደግ፣ ሕዝብን ከብተና ለማዳንና ልጆቻችን ሉአላዊት ኢትዮጵያን እንዲወርሱ ስንል የመጨረሻውን የመከላከል አማራጭ ወስደናል” ስሊም አስታውቀዋል ።
“አሁንም እያደረግን ያለነው የመከላከል ውጊያ ይኼንን ታሪካዊ አደራ ለመወጣትና ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ከአደጋ ለመከላከል ያሰበ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
“የገጠመን ወረራ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከሚፈለግብን በላይ አድርገናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “የእኛን ጥረት በተገቢ መንገድ የሚያወድስና የሌላኛው ወገን እምቢታ በተገቢው ልክ የሚያወግዝ ግን ጥቂት ነው” ብለዋል።
“ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሰላምን የሚመርጡት፣ ጦር ለመያዝ ስለማይችሉ አይደለም፤ ሰላምን ስለሚመርጡ ብቻ ነው፤ ለሰላም የዘረጋነው እጅ ምንም ዋጋ ስላላገኘ ጦር እንዲይዝ እየተገደደ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል ።
በተለያዩ አካባቢዎች፣ በከተማና በገጠር፣ በአርሶና በአርብቶ አደር መንደሮች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር፣ በመሐልና በግንባር ሆነው የመስቀል በዓል ለሚያከብሩ ኢትዮጵያውያንም “ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በሁለት እጆቿ እየሠራች ፈተናዋን ትሻገራለች” ሲሉም አረጋግጠዋል።
“በአንድ እጇ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚገባ አስጠብቃ ችግሯን ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ትታገላለች።፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝባችን በወዙ ጎተራው እንዲሞላ፤ ምሳውን በብድር ሳይሆን ከራሱ ማሳ ዘግኖ እንዲመገብ የሚችልበትን ስትራቴጂ ነድፈን መንቀሳቀስ እንጀምራለን” ሲሉም ገልጸዋል።