የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያለአግባብ የተጠቀሙ 4 የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተከሰሱ
ዐቃቤ ህግ የፖሊስ አባላቱ አዋጁን ተገን በማድረግ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ መስርቶባቸዋል
ተከሳሶቹ አዋጁን ተገን በማድረግ ህገወጥ እስር መፈፀማቸውና በማስገደድ 260 ሺህ ብር መቀበላቸው ተነግሯል
ዐቃቤ ህግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ የሙስና ወንጀል በፈጸሙ አራት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ክስ መሰረተ።
የፖሊስ አባላቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ ህገወጥ እስር በመፈፀምና በማስገደድ 260 ሺህ ብር በመቀበል ነው ክስ የተመሰረተባቸው።
የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረደዳው ከሆነ ተከሳሾቹ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የአስተዳደር ልማት ዘርፍ በሹፌርነትና በጉዳይ አስፈጻሚነት የሥራ መደብ ላይ የሚሰሩት 1ኛ ረ/ኢ/ር ፍቃዱ ዘዉዴ፣ 2ኛ. ረ/ኢ/ር ይስሀቅ ዳካ፣ 3ኛ ረ/ኢ/ር ደሴ ደጆ እና በልዩ ወንጀል ተካፋይነት ግብረ አበር የሆነው ዳዊት ዳዲ ናቸው።
ተከሳሾቹ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ዲያፍሪክ ሆቴል አካባቢ የግል ተበዳይ በባለቤትነት በሚያስተዳድረው የንግድ መደብር በመግባት 4ኛ ተከሳሽ የመረጃ መረብ ደህንነት አገልግሎት ባልደረባ በመምሰል ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተከሳሾች የፌ/ፖሊስ አባልነታቸውን ሽፋን በማድረግ ምርመራ የማከናወንና ተጠርጣሪ የመያዝ የሥራ ድርሻ ሳይኖራቸውና ምንም አይነት ትዕዛዝ ሳይሰጣቸው የግል ተበዳይን በወቅታዊ ጉዳይ ትፈለጋለህ በማለት ለሥራ በተሰጣቸው መኪና ጭነው ወስደዋል።
የግል ተበዳይን ጭነው ከወሰዱ በኋላ 1 ሚሊዮን ብር እንዲሰጣቸው ጠይቀው በኢዮጵያ ንግድ ባንክ ባልቻ አባ ነፍሶ ቅርንጫፍ 260 ሺ ብር ወደ 1ኛ ተከሳሽ የቁጠባ ሂሳብ እንዲያስገባ መከፋፈላቸውንም አቃቤ ህግ አስታውቋል።
በዚህም ተከሳሾቹ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ክስ እንደቀረበባቸው ከፍትህ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በዛሬው እለትም ተከሳሾች በችሎት ቀርበው ክሱ የተነበበላቸው ሲሆን፤ በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለመጠባበቅ ለታህሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተይዟል።