“የመቀሌውን የአየር ድብደባ በተመለከተ የተሰጠኝ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ የለም”- ተመድ
መንግስት ትናንት አርብ የህወሓትን የዉጊያ ግንኙነት ኔት ወርክ ዒላማ ያደረገ የአየር ድብደባ መፈጸሙን ማስታወቁ ይታወሳል
ተመድ ለበረራ የሚሆኑ አስፈላጊ ፈቃዶችን አግኝቶ እንደነበርም አስታውቋል
ትናንት በመቀሌ የተፈጸመውን የአየር ድብደባ ተከትሎ እርዳታ የጫኑ አውሮፕላኖቹ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ መገደዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ በሰብዓዊ ጉዳዮች እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታዎች አስተባባሪው ማርቲን ግሪፊትስ በኩል ሁኔታውን የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
መቀሌ ለማረፍ ተችግራ ተመለሰች ስለተባለችው የተመድ አውሮፕላን ጉዳይ
በመግለጫው ሁኔታው በድርጅቱ ሰብዓዊ ሰራተኞች ላይ ከፍተኛ ስጋት ማሳደሩን ግሪፊትስ ገልጸዋል፡፡
ተመድ እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረስ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ዋና አስተባባሪው የሁኔታዎች መለዋወጥ ግን ይህን አዳጋች እያደረገው ነው ብለዋል፡፡
ግሪፊትስ ተቋማቸውን ድብደባውን በተመለከተ የተሰጠውም ሆነ የደረሰው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እንደሌለ ነው በመግለጫቸው ያስቀመጡት፡፡
ለበረራ የሚሆኑ አስፈላጊ ፈቃዶችን አግኝተንም ነበር ብለዋል፡፡
የህወሓትን የዉጊያ ግንኙነት ኔት ወርክ ዒላማ ያደረገ የአየር ድብደባ መፈጸሙን መንግስት አስታወቀ
የአየር ድብደባው መቀጠሉ እና በክልሉ በቂ እርዳታዎች አለመቅረባቸው ይበልጥ እንዳሳሰበኝ ለመግለጽ እፈልጋለሁም ነው ግሪፊትስ በመግለጫቸው፡፡
ከአሁን ቀደም በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ጦርነቱ በአማራ እና አፋር ክልሎች ስለሚኖረው የከፋ ተጽዕኖ እና የንጹሃን ሞት በእጅጉ ማሰባቸውንም ነው የገለጹት፡፡
ንጹሃኑን እና መገልገያ መሰረተ ልማቶቻቸውን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባልም ብለዋል ማርቲን ግሪፊትስ፡፡
የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት አየር ኃይል ከሰሞኑ የህወሓትን የጦር መሳሪያ ማምረቻዎች፣ መጠገኛዎች የተለያዩ የግንኙነት አውታሮችን ጭምር ዒላማ ያደረጉ ተከታታይ የአየር ላይ ድብደባዎችን እየፈጸመ ነው፡፡
ትናንት አርብ ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ/ም የህወሓትን የዉጊያ ግንኙነት ኔት ወርክ ዒላማ ያደረገ የአየር ድብደባ መፈጸሙንም በአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ገጹ በኩል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ነው ተመድ እርዳታ ጭኖ ወደ ትግራይ ያመራ የነበረ አውሮፕላኔ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ተገደደ ያለው፡፡
የዐይን እማኝ እና ሰብዓዊ ሰራተኞች ናቸው ያሏቸውን የመረጃ ምንጮች ግብዓት በማድረግም ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተለያዩ ዘገባዎችን ሰርተዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተም አል ዐይን አማርኛ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ጋር የስልክ ቆይታ አድርጎ ነበር።
በቆይታው በራሳቸው ምክንያት ካሆነ በስተቀር የአየር ድብደባው እና የሰብአዊ እርዳታ ጫኝ አውሮፕላን እንቅስቃሴ አይገናኝም ያሉት ዶ/ር ለገሰ “ሰዓቱም፣ መዳረሻዎቹም የተለያዩ ናቸው” ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።