ዩክሬናውያን እና ፕሬዝዳንታቸው ለኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲታጩ ጥያቄ ቀረበ
የኖቤል ሽልማት እጩዎች የመጠቆሚያ ጊዜ ከ2 ወራት በፊት ነው በፈረንጆቹ ወርሃ ጥር መጨረሻ የተጠናቀቀው
ጥያቄው ኖቤል ህግ ጥሶም ቢሆን ዩክሬናውያንን እና ፕሬዝዳንታቸውን እጩ አድርጎ ይመዝግብ ባሉ የአውሮፓ ፖለቲከኞች የቀረበ ነው
ዩክሬናውያን እና ፕሬዝዳንታቸው ለኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲታጩ ጥያቄ ቀረበ፡፡
ጥያቄው ኖቤል ህግ ጥሶም ቢሆን ዩክሬናውያንን እና ፕሬዝዳንታቸውን ቮሎዶሚር ዜሌንስኪን እጩ አድርጎ ይመዝግብ ባሉ የአውሮፓ ፖለቲከኞች የቀረበ ነው፡፡
36 የአውሮፓ ፖለቲከኞች የፈረሙበት ይፋዊ ደብዳቤም ለኖቤል የሽልማት ድርጅት የኖርዌይ ኮሚቴ ተጽፏል፡፡
ፖለቲከኞቹ በዋናነት ከኔዘርላንድ፣ ከብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ ስዊድን፣ኢስቶኒያ፣ ሩማኒያ፣ ቡልጋሪያ እና ስሎቫኪያ የተውጣጡ ናቸው፡፡
እስከተያዘው የፈረንጆቹ ወር መጋቢት መጨረሻ ድረስ ሌሎች ፖለቲከኞችና ምሁራን ደብዳቤውን እንዲፈርሙም ተጠይቋል፡፡
ዩክሬናውያን በገጠማቸው ወረራ ሃዘኑን የሚገልጸውዓለም ከዩክሬናውያን እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከመረጡት ፕሬዝዳንታቸው ጎን የመቆሚያው ጊዜ አሁን ነው ያሉት ፖለቲከኞቹ ድርጅቱ ለሽልማቱ እጩ አድርጎ እንዲይዛቸው ጠይቀዋል፡፡
ፖለቲከኞቹ ኖቤል ህግ ጥሶም ቢሆን እጩ እንዲያደርጋቸው ነው በደብዳቤው የጠየቁት፡፡
የኖቤል ሽልማት እጩዎች የመጠቆሚያ ጊዜ ከ2 ወራት በፊት ነው በፈረንጆቹ ወርሃ ጥር መጨረሻ የተጠናቀቀው፡፡ 343 እጩዎች ተጠቁመውም ተጠናቋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 251ዱ ግለሰቦች 92ቱ ደግሞ ተቋማት ናቸው፡፡
ሆኖም ጥያቄያችን አግባብነት የጎደለውና ያልተጠበቀ እንደሆነ እናውቃለን ያሉት ፖለቲከኞቹ ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችበት አጋጣሚም ያልተጠበቀ ነው ሲሉ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የኖርዌጂያን የኖቤል ኮሚቴ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥያቄያቸውን እንዲቀበል ጠይቀዋል፡፡
የሽልማት ኮሚቴው ግን እስካሁን ለጥያቄው የሰጠው ምላሽ የለም፡፡
ለዩክሬን ተዋጊዎችን ማሰለፍ “አደጋ አለው” ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች
አሁን ላይ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኙት ዜሌንስኪ እ.አ.አ በ 2019 ነው፤ በወቅቱ የመራጩን 73 በመቶ ድምጽ አግኝተው የዩክሬን ፕሬዝዳንት የሆኑት፡፡
ስልጣን ሲጨብጡ የሀገሪቱን የፖለቲካ ድባብ እንደሚቀይሩትና ባለሙያዎችን ወደ ስልጣን እንደሚመጡ ተናግረው ነበር፡፡
ሆኖም ከሶስት ሳምንታት በፊት ዱብ እዳ ገጥሟቸው ከሩሲያ ጋር በመዋጋት ላይ ናቸው፡፡ ዩክሬናውያን ሃገራቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ ያሳሰቡት ዜሌንስኪ እርሳቸውም ወዴትም እንደማይሄዱ በመግለጽ የሃገራቸውን ጦር ለድል ለማብቃት መምራት መጀመራቸውን ገልጸው ነበር፡፡
ይህም ከዩክሬን ጎን ተሰልፈው በሩሲያ ላይ የማዕቀብ አይነቶችን ባዘነቡ ሃገራትና ሚዲያዎቻቸው ከፍተኛ ውዳሴ እና አድናቆትን አስችሯቸዋል፡፡
የሩሲያ ወረራ ለመቋቋም እና የሃገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ አመራርን እየሰጡ ነው በሚልም ብዙዎች ሲያሞካሻቸው ነበር፡፡
ሆኖም ዜሌንስኪ ለወትሮው ጎናቸው እንደሚቆሙ ቃል ሲገቡ የነበሩላቸው ምዕራባዊ ሃገራት በዋናነትም ኔቶ ጦርነቱን ብቻቸውን እንዳጋፈጧቸው ደጋግመው ሲናገሩ ነበረ፡፡
አለን ሲሏቸው ከነበሩ አካላት ሲጠብቁ የነበረውን ያህል ድጋፍ እንዳላገኙም ነበር ሲገልጹ የነበረው፡፡
አሁንም በአን ባይነታቸው የቀጠሉት የአውሮፓ ፖለቲከኞች ግን የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘት አለባቸው በሚል እጩ አድርገው አቅርበዋቸዋል፡፡