ጽ/ቤቱ በሃምዶክ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መግለጫን አውጥቷል
ከሳምንት በፊት ከሱዳን ሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የተነሱት አብደላ ሃምዶክ አሁንም በእስር ላይ መሆናቸውን ጽ/ቤታቸው ገለጸ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የአብደላ ሃምዶክን የቤት ውስጥ እስር በተመለከተ ዛሬ ዝርዝር መግለጫ አውጥቷል፡፡ ጽ/ቤታቸው እንደገለጸው ከሆነ ከአብደላ ሃምዶክ ጋር ያለው የመገናኘት ሁኔታ ውስን ነው፡፡
ነፃነትን፣ ሰላምንና ፍትህን ለማስፈን የአብዮታዊ ሃይሎች አንድነትና ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑንም ጽ/ቤቱ ጠቁሟል፡፡
በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ቮከር ፔርዝ ትናንትና በአብደላ ሃምዶክ መኖሪያ ቤት ተገኝተው ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹ ሲሆን አሁንም የቤት ውስጥ እስረኛ ሆነው እንደሚገኙ ተናግረው ነበር፡፡
ለሱዳን ችግሮች የጋራ መፍትሄዎችን በጋራ እንፈልጋለን ያሉት ልዩ መልዕክተኛው፤ በቀጣይ መፍትሄዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
አብደላሃምዶክ እና ልዩ መልዕክተኛው፤ ለሱዳን ይበጃሉ በተባሉ ቀጣይ መፍትሄዎችና የሽምግልና ሃሳቦች ላይ መነጋገራቸውን መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡
የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት መርየም አል ሳዲቅ “ሱዳን ከግልበጣው ጀምሮ በእስር ላይ ነው ያለችው” ሲሉ መናገራቸውን አል ዐይን ትናንት ዘግቦ ነበር፡፡
መርየም ግልበጣውን አካሂደው በሲቪል ይመራ የነበረውን የሃገሪቱን መንግስት ካፈረሱት የጦር ጄነራሎች ጋር እንደማይደራደሩም ነበር የገለጹት፡፡
ባለፈው ሃሙስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ሕገ መንግስታዊ ሰነዱን እና የጁባ የሰላም ስምምነትን ለመመለስ ሁሉም የሱዳን ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ውይይት እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡
የሱዳን ሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሱት የዛሬ ሳምንት ነበር፡፡
በዚህ መፈንቅለ መንግስት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አብደላ ሀምዶክ ከስልጣናቸው ተነስተው ባልታወቀ ስፍራ መታሰራቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን በመኖሪያ ቤታቸው እንደሚገኙ ጽ/ቤታቸው ገልጿል፡፡