ከአሁን ቀደም የተሰጡ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ጥቆማዎች ተቀባይነት የላቸውም ተባለ
የሀገራዊ ምክክር እጩ ኮሚሽነሮች አቀራረብ ስርዓት መዘርጋቱንም ነው ምክር ቤቱ ያስታወቀው
ጥቆማዎቹ የጥቆማ መስጫ መርሃ ግብርና ጥቆማ የሚሰጥበት ፎርማት ገና ይፋ ሳይደረግ ስለመቅረባቸው ምክር ቤቱ አስታውቋል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገራዊ ምክክር እጩ ኮሚሽነሮች አቀራረብ ስርዓት መዘርጋቱን አስታወቀ፡፡
የእጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ የሚቀበልና የሚያደራጅ የጥቆማ ተቀባይ ኮሚቴ ተቋቁሟል ያሉት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ኮሚቴው ጥቆማ ከመቀበል ጀምሮ ም/ቤቱ እስከሚሾሙ ድረስ የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ገልጸዋል፡፡
በኮሚቴው የምክር ቤቱ ጽ/ቤት ሰብሳቢ ሄኖክ ስዩምን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ሁለት አባላት መካተታቸውንም አፈ ጉባኤው አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ታገሰ ገለጻ የጥቆማ አቀባበል ሂደቱን ግልጽ፣ አሳታፊ፣ ተዓማኒ እና ከአድሎ የጸዳ ለማድረግ የሚያግዝ አማካሪ ቡድንም ተቋቁሟል፡፡
ምክር ቤቱ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ
አማካሪ ቡድኑ በራሳቸው በአቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ ሲሆን፤ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የሲቪክ ማህበራት ጥምረት ተወካይ በአባልነት ተካተውበታል፡፡
የተለያዩ ተግባራትና ኃላፊነቶች የተሰጡት አማካሪ ቡድኑ ከቀረቡ እጩዎች ውስጥ በአዋጁ ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶች በከፍተኛ ደረጃ የሚያሟሉትን እጩዎች በመለየት ረገድ አፈ ጉባኤውን ማማከር ዋነኛው ተግባሩ ስለመሆኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ በተደረገ ውይይት መጠቆሙን ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
የጥቆማ መስጫ መርሃ ግብርና ጥቆማ የሚሰጥበት ፎርማት ገና ይፋ ሳይደረግ ጥቆማዎች እየቀረቡ ስለመሆኑ አፈ ጉባኤው ገልጸው፤ ነገር ግን እነዚህ ጥቆማዎች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ተናግረዋል፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮች ማቅረቢያ ጊዜ፣ ፎርማትና አጠቃላይ የእጩዎች አቀራረብ ስርዓትን በተመለከተ አፈ-ጉባኤው ዛሬ ከሰአት በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡