በጅንካ እና አካባቢው በሚገኙ ከተሞች የተከሰተው ምንድን ነው?
የአሪ ማህበረሰብ በዞን ይተዳደር በሚል መነሻ በተፈጠረው ግጭት በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል
እስካሁን ጅንካ ከተማን ጨምሮ በአራት ከተሞች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተገልጿል
ደቡብ ኦሞ ዞን በደቡብ ክልል ካሉ ዞኖች መካከል አንዷ ስትሆን፤ ጅንካ ከተማ ደግሞ የዚህ ዞን አስተዳድር ዋና መቀመጫ ነች።
በዚህ ዞን ስር ባሉ ወረዳዎች ውስጥ ከሚኖሩ ማህበረሰቦች መካከል ደግሞ የአሪ ማህበረሰብ አንዱ ሲሆን፤ ይህ ማህበረሰብ በራሱ ዞን እንዲተዳደር የዞንነት ጥያቄ ለደቡብ ኦሞ ዞን እና ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ጥያቄ አቅርቦም ነበር።
ይሁንና ይህ የዞንነት ጥያቄያችን አልተፈታም በሚል የአሪ ማህበረሰብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ግጭት መቀስቀሱን አል ዐይን አማርኛ ከነዋሪዎች አረጋግጧል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የጅንካ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፤ የአሪ ማህበረሰብ የሚገኙባቸው ወረዳዎች ወደ ዞን ይደግ በሚል መነሻነት በደቡብ ኦሞ ዞን ሁከት መከሰቱን ተናግረዋል።
ሁከቱ ጅንካን ጨምሮ የአሪ ማህበረሰብ በሚኖሩባቸው ሶስት ወረዳዎች ላይ ከትናንት 9 ሰዓት ጀምሮ ማንነቶችን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መሰንዘራቸውን የተናገሩት ነዋሪው፤ ለብዙ ዓመታት የተለፋባቸው ንብረቶች የዘረፋ እና በእሳት ማውደምን ጨምሮ ድብደባ ተፈጽሟልም ብለዋል።
የአሪ ማህበረሰብ ወደ ዞን እንዲያድግ እንታገላለን የሚሉ አካላት በትናንትናው እለት በጅንካ ከተማ ባለ አንድ ማረሚያ ቤት ያሉ ታራሚዎችን በሀይል ለማስለቀቅ በተደረገ ሙከራ የፀጥታ ሀይሎችን ጨምሮ የሰዎች ህይወት ማለፉን አስተያየታቸውን ሰጪው ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ከትናንት ማለትም ቅዳሜ ከሰዓት ጀምሮ ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተዋል ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ አሁን ላይ በርካቶች በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው እንደሚገኙም አክለዋል።
አሁን ላይ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች መከላከያ ሰራዊት መግባት መጀመሩን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው ችግሩ ሰፋ ያለ እና በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስቸግር ደረጃ ላይ መድረሱን ነግረውናል።
የአሪ ማህበረሰብ በሚኖሩባቸው ወረዳዎች በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከእኛ ውጪ የሆኑ ብሄሮች ውጡልን የሚሉ ሃሳቦች በስፋት በመነሳት ላይ መሆናቸውን አስተያየታቸውን የሰጡን የጅንካ ከተማ ነዋሪ ገልጸዋል።
በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዳ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት፤ በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን ስር ካሉ ወረዳዎች መካከል አንዱ የሆነው የአሪ ማህበረሰብ ወረዳ ወደ ዞን እንዲያድግ በማህበረሰቡ ጥያቁ ከቀረበ ቆይቷል።
በክልሉ ውስጥ ወደ ዞንነት እንዲያድጉ ጥያቄ ያቀረቡ ወረዳዎች ብዙ ናቸው የሚሉት አቶ አለማየሁ፤ የአሪ ማህበረሰብም ጥያቄ ካቀረቡ ወረዳዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
ይሁንና እነዚህ ጥያቄዎች ከህልውና ዘመቻው፣ ከሀገር አቀፉ ምርጫ እና ከሌሎች ሀገራዊ ጥሪዎች በኋላ የመፍታት እቅድ ክልሉ አቅጣጫ ማስቀመጡን አክለዋል።
ይህ የስራ አቅጣጫ ጥያቄዎቹን ካቀረቡት አካላት ጋር ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የአሪ ማህበረሰብ ጥያቄው አሁኑኑ ይፈታ ሲል ክልሉ ደግሞ ቆይ ሲል ጥያቄውን በሀይል ለመፍታት በተደረገ እንቅስቃሴ ምክንያት በጅንካ ከተማ እና ሌሎች አራት ከተሞች ላይ የጸጥታ መደፍረስ ማጋጠሙን አቶ አለማየሁ ነግረውናል።
የአሪ ወረዳ ወደ ዞን ማደግ አለበት በሚል የተጀመረው የሀይል እንቅስቃሴ በጅንካ፣ ቶልታ፣ሜጼር፣ ጋዘር እና ወብ አሪ ከተሞች ላይ የጸጥታ መደፍረስ መከሰቱን የተናገሩት አቶ አለማየሁ፤ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ገልጸዋል።
በተወሰኑ አካባቢዎች በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን እና የሕዝብ መጓጓዣ መንገዶችን ለመዝጋት መሞከሩን የሚናገሩት አቶ አለማየሁ፤ አሁን ላይ ሁከቱን መቆጣጠር ተችሏልም ብለዋል።
የአሪ ወረዳን ወደ ዞንነት ለማሳደግ በሚል የተጀመረውን የሀይል እርምጃ ለመቆጣጠር የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የደቡብ ክልል ልዩ ሀይል እና ፖሊስ ወደ አካባቢዎቹ መግባቱንም ሃላፊው አክለዋል።
በአካባቢዎቹ በሚኖሩ በሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተሰነዘሩ ነው ይባላል በሚል ለአቶ አለማየሁ ለቀረበላቸው ጥያቄ “በጅንካ ፣በቶልታ እና በሜጸር ከተሞች የቡድን ጸቦችን ለማስነሳት ተሞክሮ ነበር ይሁንና ጉዳዩን በቁጥጥር ስራ ማዋል ተችሏል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በዞኑ በተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ በሰዎች ላይ እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ያሉት አቶ አለማየሁ የሞቱ ወይም የቆሰሉ ሰዎችን ብዛት ከመናገር ተቆጥበዋል።