አቦይ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ትናንት በቁጥጥር ስር የዋሉ የሕወሓት አመራሮች ከነበሩበት ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል
አቦይ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ዘጠኝ የሕወሓት አመራሮች ዛሬ በህግ ወደሚዳኙበት ስፍራ ደርሰዋል ሲል መከላከያ ሠራዊት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ማረፊያ ገብተዋል፡፡
የሕወሓት ቡድን “መሪና ስምሪት ሠጪው” አቶ ስብሃት ነጋ /አቦይ ስብሃት/ ሠው ሊደርስበት በማይችልበት የተከዜ በረሃ የዝንጀሮ ገደል በሚባል ቦታ መያዛቸው በትናንትናው ዕለት ታህሣሥ 30 ቀን 2013 ዓ.ም መገለጹ ይታወቃል፡፡
እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ በተገለጸው ስፍራ በሌላ ሰው እገዛ መግባታቸው የገለጸው ሠራዊቱ ከተደበቀበት በረሃ በቁጥጥር ስር አውሎ ተሸክሞ ማውጣቱን ይፋ አድርጓል፡፡
አቦይ ስብሃትን ጨምሮ ሌ/ኮ አፀዱ ሪች ፣ ኮ/ል ክንፈ ታደሠ ፣ኮ/ል የማነ ካሕሳይ ፣ አቶ አስገደ ገ/ክርስቶስ ፣ አቶ አምደማርያም ተሠማ ፣ ኮማንደር በረሄ ግርማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና የሜ/ጀነራል ሀየሎም አርአያ ባለቤት የነበረችው ወ/ሮ አልጋነሽ መለስ ከገደል ላይ ወድቃ መሞቷ መረጋገጡን የሠራዊቱ ኃይል ሰምሪት መምሪያ ኃላፊ ብ/ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው መናገራቸው ይታወሳል።