የ34 አመቱ ኦዚል በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱ ለተጫወተባቸው ክለቦች እና ተጫዋቾችም ምስጋናውን አቅርቧል
የቀድሞው የመድፈኞቹ አማካይ መሱት ኦዚል ከእግር ኳስ ራሱን ማግለሉን ይፋ አድርጓል።
ኦዚል በ34 አመቱ ከፕሮፌሽናል እግር ኳስ ራሴን አግልያለሁ ያለው በኢንስታግራሙ ገጹ ላይ ነው።
“ላለፉት 17 አመታት ፕሮፌሽናል ተጫዋች ሆኖ የመዝለቅ እድል አግኝቻለሁ፤ ለዚህ እድልም በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገጠመኝ ጉዳት ግን ከእግር ኳሱ አለም ራሴን ገለል ማድረግ እንዳለብኝ አሳይቶኛል” ብሏል ተጫዋቹ።
ኦዚል በጥር ወር 2021 ከሚኬል አርቴታ ጋር መግባባት ባለመቻሉ መድፈኞቹን መሰናበቱ ይታወሳል።
በኢንስታግራም ገጹ ላይ ባሰፈረው የስንብት መልዕክት ግን ከሻልከ አንስቶ በዌርደር ብሬመን፣ ሪያል ማድሪድ፣ አርሰናል፣ ፌነርባቼ እና ባሳክሼር ላሰለጠኑት ባለሙያዎች እና የቡድን አጋሮቹ ምስጋናውን አቅርቧል።
በፈረንጆቹ 2013 ከሪያል ማድሪድ በ42 ሚሊየን ዶላር አርሰናልን የተቀላቀለው መሱት ኦዚል ከመድፈኞቹ ጋር አራት የኤፍ ኤ ዋንጫ አንስቷል።
የላሊጋ እና ኮፓ ዴላሬ ዋንጫን ከሪያል ማድሪድ ጋር ያነሳው ኦዚል በ2014ትም ከጀርመን ብሄራዊ ቡድን ጋር የአለም ዋንጫን መሳሙም የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ ተጫዋቹ በ2018 ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ጋር መታየቱን ተከትሎ የጀርመን ጋዜጦች ጉዳዩን ከዘረኝነት ጋር አገናኝተው ሲያራግቡት እንደነበር ጎል ዶት ኮም አስታውሷል።
ኦዚል የጀርመን ፖለቲከኞችን ከሚወርፉት ኤርዶሃን ጋር ፎቶ መነሳቱ ያስቆጣቸው ጀርመናውያን ውለታውን ረስተው የዘር ግንዱን መመርመር ሲይዙ ተጫዋቹም ራሱን ከብሄራዊ ቡድኑ ማግለሉ አይዘነጋም።
በአርሰናል የማይረሳ ጊዜን ያሳለፈው ኦዚል በቀጣይ እንደ አርቴታ በአሰልጣኝነት ይመለስ ወይ በሌላ ሙያ ያተኩር ያለው ነገር የለም።
“አሁን ለሁለት ሴት ልጆቼ ጊዜ መስጠትን መርጫለሁ፤ በቅርቡ እንገናኛለን” ሲልም መልዕክቱን ቋጭቷል።