ህወሓት በአፋር ዳግም በከፈተው ጥቃት ከ220 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን የክልሉ መንግስት አስታወቀ
ህወሓት በክልሉ ኪልበቲ ረሱ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሶስት ወረዳዎችን መቆጣጠሩንም የክልለሉ መንግስት አስታውቋል
ህወሓት ከወረራቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ እንዲወጣና የከፈተውን ጦርነት እንዲያቆም የአፋር ክልል መንግስት አሳሰቧል
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በአፋር ክልል ላይ ዳግም በከፈተው ጥቃት ከ220 ሺህ በላይ ዜጎች ማፈናቀሉን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ፤ "ለሰላም ስል ወጥቻለሁ የሚለው ህወሓት ወሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች እንዲወጣ ቢደረግም በማግስቱ ከታህሳስ 10 ቀን 2014 ጀምሮ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የደረሰበትን ኪሳራ ለማካካስ እና ለመበቀል በኪልበቲ ረሱ በአብኣላ በኩል እና በተለያዩ ወረዳዎች ጥቃቶችን ማድረሱን እንደቀጠለ ነው” ብሏል።
“ህወሓት ከባድ መሳሪያ ወደ ንፁሀን ዜጎች በመተኮስ ህይወት እየቀጠፈ እና ሆስፒታሎች፣ የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶችን ኢላማ ያደረገ የከባድ መሳሪያ ድብደባ እየፈፀመ ነው” ሲልም የክልሉ መንግስተ አስታውቋል።
“ከሰሞኑም በተደራጀ መልኩ በአብአላ፣ በመጋሌና ኤረብቲ ወረዳዎችን በመቆጣጠር እና በራህሌ ወረዳንም ከፊል ቀበሌዎች ድረስ ዘልቆ በመግባት ከባድ ጥቃት ከፍቶ ንፁሀንን በመግደል እና በማሳደድ ወረዳዎቹን እያወደመ ነው” ሲልም አስታውቋል።
በህወሓት ዳግም ወረራም ከ220 ሺህ በላይ ንጹሃን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንም የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።
መግለጫው አክሎም “ህወሓት የራሱን እድሜ ከማራዘም ውጭ ጭራሽ ቅንጣት ታክል ለህዝብ ሰብአዊነት የሚሰማው አለመሆኑን በመግለፅ፤ በኪልበቲ ረሱ በኩል ለትግራይ ህዝብ ይደርስ የነበረውን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲስተጓጎል አካባቢው የጦርነት ቀጠና እንዲሆን ተደጋጋሚ ጥቃት መፈፀሙን ለአብነት አንስቷል
“ህወሓት ርሀብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም እና የፖለቲካ ትርፍ በመፈለግ እየፈጸመ ካለው የሽብር ተግባሩ እንዲወጣ የአለም ማህበረሰብ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት እና የሽብር ቡድኑ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸውን የውሸት ማወናበጃ መግለጫዎችን ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን እውነታ በመረዳት ይህን ድርጊቱን በቃ እንዲል” ጥሪ አቅርቧል።
የክልሉ መንግስት ከተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመስራት ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ ባለፉት ሶስት አመታት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ለአብነት ጠቅሷል።
“የክልሉ መንግስትም ሆነ የአፋር ህዝብ ለትግራይ ህዝብ በቡድኑ ወረራና ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር የሚሰራ ይሆናልም”ብሏል።