ኮሚሽነሩ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነው በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት
የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
በፌዴራል ፖሊስ በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ መምሪያ ሀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ለኢቲቪ እንዳሉት፣ ኮሚሽነሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነው።
አቶ ምትኩ ካሳ ኤልሻዳይ ከተሰኘ በጎ አድራጎት ማህበር ባለቤት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል በሚል በመጠርጠራቸውንም ነው ፖሊስ ያስታወቀው።
ኤልሻዳይ የተሰኘው ድርጅት በአዋሽ፣ በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ በእንጅባራ እና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈናቃዮች በሌሉበት ተፈናቃዮች አሉ በማለት በተደጋጋሚ ጊዜ የእርዳታ እህልና አልባሳት በመረከብ ሽጦ ለተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት መግዛቱ በምርምራ መረጋገጡን ነው ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ የተናገሩት።
ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ሰፊ ክትትል ሲያደርግ እንደነበረም ረዳት ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
ምትኩ ካሳ ማን ናቸው
ምትኩ ካሳ ጉትሌ በይርጋለም ከተማ ነው ተወልደው ያደጉት፡፡ ከያነው ዓለምማያ ዩኒቨርስቲ በግብርና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአኳ ካልቸር ከኔዘርላንዱ ወገኒንገን ግብርና ዩኒቨርስቲ በ1998 አግኝተዋል፡፡
በፕላን እና ልማት ኮሚሽን ጀማሪ ባለሙያ ሆነው ስራ የጀመሩት አቶ ምትኩ እስከ ከፍተኛ ባለሙያነት ደርሰው በአርብቶ አደር አካባቢዎች ፖሊሲ ጉዳይ ኃላፊነት፤ በኋላም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ ሆነው የሰሩም ሲሆን ከፈረንጆቸሁ 2008 ጀምሮ በግብርና ሚኒስቴር የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ሚኒስትር ዴዔታ በመሆን ሰርተዋል፡፡
በ2015 ደግሞ የብሔራዊ አደጋ እና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር በመሆን ኢትዮጵያ በኤል ኒኖ ድርቅ ጭምር በተፈተነችበት ጊዜ አገልግለዋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሃፊ የውስጥ ተፈናቃዮች ከፍተኛ ፓናል አማካሪ ሆነው ጭምር ያገለገሉት አቶ አቶ ምትኩ በሙስና ተጠርጥረው ተያዙ እስከተባሉበት ጊዜ ድረስ ብሔራዊ አደጋ እና ስጋት ስራ አመራርን በኮሚሽነርነት ሲመሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡