ሩሲያ፤ ፑቲንና ዘለንስኪ የሚገናኙበት ምክንያት እንደሌለ አስታወቀች
ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች መገናኘት ካለባቸው እንኳን ተደራዳሪዎች ስራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ነው ተብሏል
ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች መገናኘት ካለባቸው እንኳን ተደራዳሪዎች ስራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ነው ተብሏል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭለድሚር ፑቲን እና የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሊገናኙ የሚችሉበት ምክንያት እንደሌለ ክሬምሊን አስታወቀ፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፒስኮቭ ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር የሚገናኙበት ምንም መሰረት እንደሌለ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
ፒስኮቭ መሪዎቹ መገናኘት ካለባቸው እንኳን የሚገናኙት የተሰየሙት ተደራዳሪዎች ስራቸውን ከሰሩ በኋላ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን ከጦርነት በኋላ ድርድር የጀመሩ ቢሆንም እስካሁን ግን ትልቅ ለውጥ ያመጣ ውሳኔ አልተወሰነም፡፡
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን ጦርነት ውስጥ የገቡት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ተነናኝተው እንዲመክሩ ሀሳብ አቅርበው ነበር፡፡
ይሁንና ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፒስኮቭ፤ ፑቲን ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር ሊነጋገሩ ቢችሉ እንኳን ተደራዳሪዎች የተሰጣቸውን የቤት ስራ ሰርተው ካጠናቀቁ በኋላ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ሁለቱም ወገኖች የተጀመረው ድርድር ውጤት አለማምጣቱን ቢናገሩም ውጤት ላለመገኘቱ ግን እርስ በእርስ ግን እየተወነጃጀሉ ነው፡፡
ዲሚትሪ ፒስኮቭም አሁን ላይ እየተደረገ ያለ ንግግር እንደሌለና ለዚህም ተጠያቂዎቹ ዩክሬንን የወከሉ ተደራዳሪዎች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
“አሁን ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር መገናኘታቸው አስፈላጊ አይደለም” ያሉት የፑቲን ቃል አቀባይ፤ በዩክሬንም ሆነ በሩሲያ ወገን ያሉት ተደራዳሪዎች ስራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ምናልባት ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች የመገናኘት ዕድል ሊኖራቸው ይችላል ብለዋል፡፡
ሞስኮ እና ኪቭ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ይፋዊ ድርድር ጀምረው የነበረ ቢሆንም ዩክሬን፤ የሩሲያ ኃይሎች ከክሪሚያ ጭምር እንዲወጡ ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ አሌክሰይ አርስቶቪች ሀገራቸው፤ የሩሲያ ወታደሮች ከክሬሚያ እና ዶንባስ ግዛቶች እንዲወጡላት እንደምትፈልግ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡