ተማሪዎቹ እገታውንና ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ አስመልክቶ በወልዲያ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል
በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ የራያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማይጨው ከተማ የሚገኘውን ዩኒቨርስቲያቸውን ለቀው አጎራባች ወደሆኑ ወልዲያን መሰል የአማራ ክልል አካባቢዎች መጥተዋል፡፡
በቁጥር 220 ገደማ ነን የሚሉት ተማሪዎቹ ባደረባቸው ስጋት ምክንያት ዩኒቨርስቲያቸውን ባሳለፍነው ሰኞ ማለትም ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ/ም እኩለ ሌሊት ላይ ለቀው በእግር ጉዞ መሆኒ ከዚያም በአላማጣ አድርገው ወልዲያ በተሸከርካሪ መግባታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርስቲውን ለቀው ከወጡ ተማሪዎች መካከል አንዷ የ3ኛ ዓመት የስነ ዜጋ እና ስነ ምግባር ተመራቂ ተማሪዋ ስንዱ ገበያው ናት፡፡
ለቀን ከወጣነው አብዛኞቻችን ተመራቂዎች ነን የምትለው ተማሪ ስንዱ ዩኒቨርስቲውን ሲጠብቅ የነበረው መከላከያ በድንገት ግቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ እኛም ለደህንነታችን ዋስትና ባለመኖሩ እኩለ ሌሊት ላይ ለቀን ወጥተናል ስትል ትናገራለች፡፡
እስከ መሆኒ በእግራቸው ከዚያም ከተማው ሳይገቡ በአቋራጭ መንገድ ሲጓዙ የሚሳፈሩበት ተሽከርካሪ አግኝተው ወደ አላማጣ ማቅናታቸውንም ነው የምትገልጸው፡፡
በጉዟቸው ለመሆኒ እስከተቃረቡበት ጊዜ ድረስ አብረዋቸው ሲጓዙ የነበሩና ውሃ ለመጠጣት በሚል ወደኋላ የቀሩ 7 ተማሪዎች መንገድ ላይ ታግተው ተለይተው መቅረታቸውንም ትናገራለች፡፡
ይህን ታግተው ከነበረበት አምልጠው ከመጡና ንብረታቸው መወሰዱን ከተናገሩ ሶስት ተማሪዎች ማረጋገጧን የተናገረችው ተማሪዋ ቀሪዎቹ 4 ታጋች ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አለመቻሏንም ተናግራለች።
አሁን ላይ በጊዜያዊነት በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ከዚያም በሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ግቢ ማረፋቸውን የምትገልጽም ሲሆን ከዩኒቨርስቲያቸው ሳይወጡ የቀሩ ተማሪዎች ሁኔታ እሷንም ባልደረቦቿንም እንዳሳሰባቸውና መውጣታቸውን እስከሚያረጋግጡ ድረስ ባሉበት እንደሚቆዩም ገልጻለች፡፡
2ኛ ዓመት የማኔጅመንት ተማሪ ነበርኩ የሚለው መሃመድ አህመድ ይህንኑ ሁኔታ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጿል፡፡
እስካሁን ግቢ መቆየት የቻልነው መከላከያው ሲጠብቀን ስለነበር ነው የሚለው መሃመድ የመከላከያውን መውጣት ተከትሎ ለደህንነታቸው በመስጋትና ዋስትና የሚሰጣቸው አካል በማጣት ግቢውን ለቀው መውጣታቸውንና እስከ መሆኒ በእግራቸው፤ እስከ አላማጣና ወልዲያ ደግሞ በተሽከርካሪ መምጣታቸውን ይናገራል፡፡
“ከአሁን ቀደምም ለምን መጣችሁ የሚሉን፤ ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ ወደ ዩኒቨርስቲው የሚመለሱ ስለታማ መሳሪያዎችንም ጭምር የሚይዙ የዩኒቨርስቲ ጓደኞቻችን ነበሩ”ም ነው የሚለው፡፡
ይህንን በመስጋት ግቢውን ለቀው በመጓዝ ላይ ሳሉ 7 ተማሪዎች መታገታቸውንና ሶስቱ ንብረታቸው ተወስዶ መለቀቃቸውንም አረጋግጧል፡፡
መሃመድ ከግቢ ሳይወጡ የቀሩ ብዙ ጓደኞቻችን አሉ የሚለው ይህ ተማሪ መንግስት በአፋጣኝ ለተማሪዎቹ ሊደርስላቸው እና ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ችግሮች ሊታደጋቸው እንደሚገባ ይጠይቃል፡፡
የ3ኛ ዓመት የኤሌክትሪካል ምህንድስና ተማሪው ይህዓለም መታደል ታግተው ተለቀቁ ከተባሉት ሶስት ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
መሆኒ ከተማ አቅራቢያ ውሃ እንጠጣ ብለን አብረውን ሲጓዙ ከነበሩ ተማሪዎች ተለይተን በገባንበት አካባቢ ታግተናልም ይላል፡፡
“አጋቾቻችን ገጀራና ሌሎችንም ስለታማ መሳሪያዎች የያዙ ሰባት ‘ወያላዎች’ ናቸው” የሚለው ይህዓለም በወያላዎቹና አብረዋቸው በነበሩ ግበራበሮቻቸው ተደብድበው የእጅ ስልኮቻቸውንና ሌሎችንም ንብረቶቻቸውን መቀማታቸውን ተናግሯል፡፡
በዚህ መካከል እሱን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ታጋቾች ሮጠው ማምለጣቸውንና ወደ አካባቢው ተመልሶ ወደመጣው መከላከያ ኃይል መጠጋታቸውን ሌሎቹ ታጋቾች ደግሞ ወደ ጫካ መወሰዳቸውንም ነው የሚናገረው፡፡
“አሁን ምን ማድረግ እንዳለብን አላወቅንም ግራ ገብቶናል” የሚልም ሲሆን ታጋቾቹም ሆኑ ግቢ የቀሩት ተማሪዎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡
ተማሪዎቹ ሁኔታውን በማስመልከት ዛሬ በወልዲያ ከተማ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ በሰልፉ ሳይወጡ ስለቀሩና ስለታገቱ ተማሪዎች ደህንነት ጉዳይ ጠይቀዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ የዩኒቨርስቲውን የአስተዳደር አካላት ስለ ሁኔታው ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት በስልክ አድራሻቸው ሊገኙ ባለመቻላቸው ምክንያት አልተሳካም፡፡
ስለ ሁኔታው የጠየቅናቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ አመለወርቅ ህዝቄል በራያ ዩኒቨርስቲ ብቻም ሳይሆን በትግራይ ክልል በሚገኙ በሌሎቹም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጉዳይ ላይ ምክክር እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ለተማሪዎቹ ደህንነት ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት፡፡
የልጆቻቸው ሁኔታ ያሳሰባቸው በርከት ያሉ የተማሪ ቤተሰቦች በአዲስ አበባ በሚኒስቴሩ ቢሮ ተገኝተው ስላሁኔታው ምላሽ እንዲሰጣቸው በመጠየቅም ላይ ይገኛሉ፡፡