አዲሱ ተመራጭ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥቅምት 2023 ድረስ በስልጣን ላይ ይቆያሉ ተብሏል
የቀድሞው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሻሪፍ ታናሽ ወንድም የሆኑት ሸህባዝ ሻሪፍ አዲሱ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርገው በሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት ተሹመዋል።
የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራን ካሃን በሀገሪቱ ፓርላማ የመተማመኛ ድምፅ በማጣታቸው ከትናንት በስቲያ ከስልጣን መነሳታቸው ይታወሳል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን አመራር ላይ የመተማመኛ ድምጽ የመስጠት ሂደት የተካሄደው ከትናንት በስቲያ እኩለ ሌሊት ላይ ሲሆን፤ ድምጽ የተሰጠው ተቃዋሚዎቻው በእርሳቸው ላይ ሞሽን ካቀረቡ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥ የሚጠይቀው ሞሽን ባሳለፍነው ሳምንት ቀርቦ የነበረ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ብላው ፓርላማውን በመበተናቸው ሳይካሄድ ቆይቶ ነበረ።
የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍድር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን ከህገ መንግስቱ ውጪ ፓርላማውን በትነዋል በሚል ውሳኔያቸውን ውድቅ ማድረጉት ተክሎም ፓርላማው ተሰብስቦ ድምጽ ሰጥቷል።
ይህንን ተከትሎም ኢምራን ካሃን በፓርላማው የመተማመኛ ድምጽ በማጣታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ተነስተዋል።
ኢምራን ካሃን በፓኪስታን ታሪክ የመተማመኛ ድምጽ በማጣት ከስልጣናቸው የተነሱ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናውም ተዘግቧል።
የፓኪስታን ፓርላማ ኢምራን ካሃንን ተክተው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑትን ሰው ዛሬ መርጧል።
በኢምራን ካሃን ቦታ የተመረጡት ሸህባዝ ሻሪፍ በሀገሪቱ ምርጫ እስከሚደረግበት የፈረንጆቹ ጥቅምት 2023 ድረስ በስልጣን ላይ ይቆያሉ ተብሏል።
የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን ባሳለፍነው ቅዳሜት “ተቃዋሚዎቼ ከአሜሪካ ጋር እያሴሩ ሊገለብጡኝ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።