በበዓለ ሲመቱ ላይ የየትኞቹ ሃገራት መሪዎች ተገኙ?
ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያን ለቀጣዮቹ 5 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ይመሩ ዘንድ ዛሬ መመረጣቸው የሚታወቅ ነው
ከአልጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራማታን ላማምራ እና ከዲ አር ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር በተጨማሪ የ6 ሃገራት መሪዎች በበዓለ ሲመቱ ታድመዋል
ኢትዮጵያን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራው አዲስ መንግስት ዛሬ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ/ም መመስረቱን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት የተለያዩ ሃገራት መሪዎች ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
መሪዎች ከትናንት እሁድ ጀምሮ ነው ወደ አዲስ አበባ መግባት የጀመሩት፡፡
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አማካሪያቸውን ፌሚ አዴሲናን ቀድመው ወደ አዲስ አበባ የላኩት የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት መሃመዱ ቡሃሪ የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ሚኒስትሮቻቸውን ያካተተ ልዑክ ይዘው ትናንት ማምሻ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱ ጊዜም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና በሌሎች ሚኒስትሮች አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከደቂቃዎች በፊት በተጀመረው የበዓለ ሲመት ስነ ስርአት ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳልም ትናንት ማምሻ አዲስ አበባ ከገቡ የአፍሪካ መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማኪ ሳል ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱ ጊዜ ተቀብለዋቸዋል።
የኢትዮጵያ አዲስ መንግሥት ምስረታ እተካሄደ ነው
የኬንያ፣ የኡጋንዳ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የጅቡቲ እና የሶማሊያ መሪዎች ደግሞ ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ቦሌ ሲደርሱ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ በትምህርት ሚኒስትሩ ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የኡጋንዳውን ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒን፣ የደቡብ ሱዳኑን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲትን፣ የጂቡቲውን ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌን እንዲሁም የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ጃን ሚሼል ሳማ ሉኮንዴን የተቀበለው ይኸው የገንዘብ እና የትምህርት ሚኒስትሩን ያካተተው የኢትዮጵያ ልዑክ ነው፡፡
የአልጄሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታን ላማምራም በበዓለ ሲመቱ ለመታደም አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ላማምራ አዲስ አበባ በደረሱ ጊዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴዔታ ሬድዋን ሁነሴን አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
አጋጣሚው ከተለያዩ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ባለስልጣናት ጋር በጸጥታና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ለመምከር እንደሚያመችም ነው በአዲስ አበባ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋር መወያየታቸውን ያስታወቁት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
“በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከማንም ጋር ምንም አይነት ድርድር አይኖርም”- ፕሬዝዳንት ሣሕለ ወርቅ
የአዲሱ መንግስት ምስረታ ዛሬ ጠዋት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
ዐቢይ አህመድም ኢትዮጵያን ለቀጣዮቹ 5 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ይመሩ ዘንድ ተመርጠዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዓለ ሲመት በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ተጋባዥ የሃገራት መሪዎችና እንግዶች በተገኙበት በመስቀል አደባባይ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ትናንትና እና ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የገቡ የሃገራት መሪዎችና ተወካዮችም በዓለ ሲመቱን በመታደም ላይ ይገኛሉ፡፡