ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጋበዙ
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንኪ ጋር በስልክ ተወያይተዋል
ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን ለኢትዮጵያ 300 ሺህ ቶን ስንዴ አቅርባለች
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጋበዙ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ጋር በስልክ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በትዊተር ገጻቸው እንደገለጹት "ዛሬ ከፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ጋር በሁለትዮሽ እና በዓለም አቀፍ የጋራ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ሰላም ለማምጣት በሚቻልበት መንገድ ላይ በስልክ ተወያይተናል" ብለዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ዩክሬንን እንዲጎበኙ መጋበዛቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
- የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የሶስተኛው የዓለም ጦርነት ፍርሃት 'ምክንያታዊ' ነው አሉ
- ቻይና በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከሞስኮ ጋር ከወገነች 3ኛው የዓለም ጦርነት ይነሳል ሲሉ ዘለንስኪ አስጠነቀቁ
ኪቭን እንዲጎበኙ የተጋበዙት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ግብዣውን ስለመቀበላቸው እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን በጦርነት ውስጥም ሆና ለኢትዮጵያ 300 ሺህ ቶን ስንዴ አቅርባለች ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ዩክሬን ተጨማሪ 90 ሺህ ቶን ስንዴ ለኢትዮጵያ እንደምታቀርብ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ለአንድ ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከ500 በላይ ቀናትን አስቆጥሯል።
ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን እንድታስወጣ እና ጦርነቱን ለማውገዝ በተጠራው የተመድ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በተደጋጋሚ ድምጸ ተዓቅቦ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በተርኪየ አሸማጋይነት ዩክሬን በጥቁር ባህር በኩል የዩክሬን ስንዴ ለዓለም ገበያ ሲቀርብ ቆይቷል።
ይሁንና ሩሲያ ከሰሞኑ ከዚህ ስምምነት ራሷን ማግለሏን ተከትሎ ዩክሬን በጥቁር ባህር በኩል ስንዴ ማጓጓዟን ለማቆም ተገዳለች።
ሩሲያ ከስምምነቱ በመውጣቷ ምክንያት የዓለም ስንዴ ዋጋ ጭማሪ በማሳየት ላይ መሆኑን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል።