ብልጽግና ፓርቲ “ልዩ ሀይሎችን እንደገና ማደራጀት ልክ ያልነበረን ጉዳይ ልክ የማድረግ ውሳኔና ጥረት ነው” አለ
“ልዩ ሀይልን ትጥቅ የማስፈታት ሳይሆን የተሻለ የማስታጠቅ፤ የመበተን ሳይሆን በጠንካራ መሰረት ላይ የማደራጀት ስራ ላይ ነኝ” ብሏል
ብልጽግና ፓርቲ “የፖለቲካ ተዋናያን ሞትን ለመጥመቅ- ግጭት ከመጠንሰስ ሊቆጠቡ ይገባል” ሲል አስጠንቅቋል
ብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱ የፖለቲካ ተዋናያን “ሞትን ለመጥመቅ- ግጭት ከመጠንሰስ ሊቆጠቡ ይገባል” ሲል አስጠነቀቀ።
መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎች እንደገና ለማደራጀት ውሳኔ በመሳለፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን ያሳወቀ ሲሆን፤ ህንን ተከትሎም በተለይም በአማራ ክልል ተቃውሞ መነሳቱ ይታወሳል።
ፓርቲው የክልል ልዩ ኃይሎች እንደገና ለማደራጀት የተደረሰውን ውሳኔ አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ “ልዩ ሀይሎችን እንደገና የማደራጀት አስፈላጊነት ልክ ያልነበረን ጉዳይ ልክ የማድረግ ውሳኔና ጥረት ነው” ብሏል።
“በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም የክልሎችን ልዩ ሃይል በሕገ መንግስቱ መሰረት መልሰን እንደምናደራጅ አቋማችን ለህዝብ ግልጽ ማድረጋችን ይታወሳል” ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።
- የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ እንቅስቃሴ ማካሄድ መጀመሩን መንግስት አስታወቀ
- የተደረሰው ውሳኔ "ለሕብረ ብሄራዊ አንድነት" ሲባል እንደሚተገበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ
በዚህ ጉዳይ ላይ ከህዝብም የክልል ልዩ ሃይሎች ሕገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ እና የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት በተሻለ መልኩ በሚያስጠብቅ አኳሃን መልሶ የማደራጀት ስራ መሰራት እንዳለበት በተለያየ መልኩ ለመንግስትና ለፓርቲው ጥያቄ ሲነሳ መቆየቱን አስታውሷል።
“በመሆኑም ውሳኔው የህዝቡን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባና ሕገመንግስታዊ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል” ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።
በሕገ መንግስቱ ላይ “ሀገርን እና ህዝብን ከየትኛውም ጥቃት እና ጠላት የሚከላከል ሀገራዊ ሀይል የመገንባት ሃላፊነት እና ስልጣን የፌዴራል መንግስቱ ብቻ እንደሆነ በግልጽ ተመልክቷል” ብሏል ፓርቲው።
የክልል መንግስታትም የክልላቸውን ሰላምና ጸጥታ የሚያስጠብቅ ክልላዊ ፖሊስ አደራጅተው እንደሚመሩ በሕገ መንግስቱ ተደንግጓል ያለው መግለጫው፤ ልዩ ሀይሎችን እንደገና የማደራጀት ልክ ያልነበረን ጉዳይ ልክ የማድረግ ውሳኔና ጥረት መሆኑ ይታወቅልኝ ብሏል።
“የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መሪዎቻቸው እንዲሁም ማህበራዊ አንቂዎች ጉዳዩን አንድን ክልል ብቻ ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ አድርገው የሚያቀርቡበትና ጉዳዩን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸው ‹‹ማክሰም፣ ማጠፍ፣ ማፍረስ፣ መበተን›› የሚሉት አገላለጾች ግባቸው ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስና ጊዜያዊ ቅቡልነት ለማግኘት የመጣር ፍላጎት እንደሆነ መረዳት ይቻላል” ብሏል።
ስለሆነም “ከዚህ ሀገርን ዋጋ ከሚያስከፍል ሕገ ወጥ እና መርሕ አልባ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ” ብልጽግና ፓርቲ አሳስቧል።
“ውሳኔው በአማራ ክልል ላይ ብቻ የተወሰነ ውሳኔ አድርገው ለማቅረብ የሚጋጋጡ ሀገር ነቅናቂ ግጭት- ናፋቂ ሀይሎች የሚነዙት መርዛማ መረጃ ፍጹም ሀሰት ነው” ሲልም ፓርቲው ነሳውቋል።
ውሳኔው ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በተመሳሳይ የጊዜ መስመር የሚተገበር እንደሆነም ገልጿል።
“ሆኖም ግን ብልጽግና ፓርቲ በተግዳሮቶች ውስጥም ቢሆን ከህዝባችን እና ከሁሉም የልዩ ሀይል አመራሮቻችና አባላት ጋር በስክነት በመወያየት እና የተፈጠረውን የተግባቦት ክፍተት በመሙላት ለሀገር እና ለህዝብ ዘላቂ ሰላም በሚበጀው ጎዳና መጓዙን ይቀጥላል።
“በዚህ አጋጣሚም ሻማ እንዲሸጥላቸው ጨለማ የሚናፍቁ እና የሚጠብቁ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መሪዎቻቸው ነገሮችን ከማባባስ እና ሞትን ለመጥመቅ- ግጭት ከመጠንሰስ ተቆጠቡ” ሲልም ፓርቲው አስጠንቅቋል።
የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፌደራል እና የክልል የጸጥታ መዋቅሮች እንዲካተቱ ወስኖ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ መጀመሩን መንግስት ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫው አስታውቆ ነበር።
ይንን ተከትሎም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎችን ጨምሮ ልሎችም የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም የመንግስት ውሳኔ ከተቃዋሚ ፖርቲዎችም የተለያየ ተቃውሞ እያስናገደ ሲሆን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ትናንት ባወጣው መግለጫ የፌደራል መንግስት በአማራ ልዩ ኃይሉ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበልና ልዩ ኃይሉም እንዳይበተን አሳስቧል።
ኢዜማ በበኩሉ ህወሓት "በአማራ ክልል ስር ያሉ አካባቢዎችን" አስመልሳለሁ እያለ ባለበት ወቅት የመንግስት "በጥድፊያ እና በድብቅ" ወደ ተግባር መግባት ወቅታዊ አይደለም፤ውጤቱም አደገኛ ነው ብሏል።