ያለመከሰስ መብት ያላቸው ሰዎች በአስቸኳይ አዋጁ ከታሰሩ በኋላ ለምን በቀጥታ ክስ መመስረት አልተቻለም?
አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ አራት የምክር ቤት አባላት ከታሰሩ ከወራት በኋላ ያለመከሰስ መብታቸው በቅርቡ መነሳቱ ይታወሳል
በአስቸኳይ አዋጁ መሰረት የምክር ቤት አባላቱ ቢታሰሩም ክስ ለመመስረት ግን ለምን መደበኛ ህጉን መከተል አስፈለገ?
ያለመከሰስ መብት ያላቸው ሰዎች በአስቸኳይ አዋጁ ከታሰሩ በኋላ ለምን በቀጥታ ክስ መመስረት አልተቻለም?
የፌደራል መንግሥት የክልል ልዩ ሀይሎችን ዳግም አደራጃለሁ ማለቱን ተከትሎ በአማራ ክልል ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ጦርነት ተከስቷል።
በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የ"ፋኖ" ታጣቂዎች መካከል የተከሰተው ግጭት ቀስ በቀስ ተባብሶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት ሆኗል።
በህዝብ ተወካዮም ምክር ቤት የታወጀው የአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደ አስፈላጊነቱ ከክልሉ ውጪም ይተገበራል መባሉን ተከትሎ ያለ መከሰስ መብት የነበራቸው የምክር ቤት አባላት ለእስር ተዳርገዋል።
ከታሰሩ የምክር ቤት አባላት መካከልም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሀንስ ቧያለው እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ካሳ ተሻገር (ዶ/ር) ዋነኞቹ ናቸው።
የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አባሉ አቶ ታዬ ደንደዓም ያለ መከሰስ መብታቸው አባል በሆኑባቸው ምክር ቤቶች ከሶስት ሳምንት በፊት ተነስቷል።
እነዚህ የምክር ቤት አባላት ለእስር የተዳረጉት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካኝነት ነው የተባለ ሲሆን ይህ አዋጅ ያለ መከሰስ መብት ያላቸውን ሰዎች የማሰር ስልጣን ለህግ አስፈጻሚዎች በመስጠቱ እንደሆነ የፍትህ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ለህዝብ ተዉካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያለ መለሰስ መብት ያላቸውን ሰዎች የህግ አስፈጻሚ አካላት እንዲያስሩ ፈቅዶላቸው ክስ ለመመስረት ግን ለምን ወደ መደበኛ ህግ መሄድ አስፈለገ? የሚሉ ሀሳቦች አከራካሪ ጉዳይ ሆኗል።
አልዐይን አማርኛ በዚህ ጉዳይ ላይ የህግ ባለሙያዎች በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ጠይቋል።
ጠበቃ እና የህግ አማካሪው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ፥ የምክር ቤት አባላቱ ያለ መከሰስ መብት ቢኖራቸውም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ለእስር መዳረጋቸውን ከፍትህ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲየስ ማብራሪያ መረዳታቸውን ነግረውናል።
እንደ አቶ ሰለሞን አስተያየት ከሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት በወንጀል ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉትን የምክር ቤት አባላትን ክስ ለመመስረት የግድ በመደበኛው ህግ ያለመከሰስ መብታቸውን ማንሳት አስፈላጊ አልነበረም።
ሌላኛው የህግ ባለሙያ አቶ አቤል ዘውዱ በበኩላቸው በአማራ ክልል እና ሌሎች አካባቢዎችም ተፈጻሚነት ይኖረዋል በሚል የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያለመከሰስ መብት ያላቸውን ሰዎች ጨምሮ በወንጀል የተጠረጠሩ ማናቸውንም አካላት በህግ ቁጥጥር ስር የማዋል መብት እንዳለው ይፈቅዳል ብለዋል።
ይሁንና ይህ ህግ ያለመከሰስ መብት ያላቸውን ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር የማዋል እንጂ ክስ የመመስረት መብት ባለመስጠቱ ያለመከሰስ መብታቸውን የግድ ማስነሳት አስፈልጎታል ሲሉ ጠበቃ አቤል ጠቅሰዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በባህሪው ለአስፈጻሚው አካል የተለጠጠ መብት ስለሚሰጥ በዚህ አዋጅ መሰረት በወንጀል ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች መብታቸው የጠበበ እና የተገሰሰ ይሆናልም ብለዋል።
ጠበቃ ሰለሞን በበኩላቸው በአዋጁ መሰረት በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመስረት የግድ ወደ መደበኛ ህጉ መመለስ ካስፈለገ እነዚህ ተጠርጣሪዎች የህግ ድጋፍ እንዳያገኙ መከልከላቸው ትክክል ሊሆን እንደማይችል ገልጸዋል።
ከሀምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው የአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት በሚል ታውጆ የነበረ ቢሆንም ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ ይታወሳል።
ይህ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊጠናቀቅ ሁለት ወር ገደማ የቀሩት ሲሆን በአማራ ክልል ጦርነቱ አሁንም በብዙ ቦታዎች እንደቀጠለ ይገኛል።
"ጽንፈኞች" ላይ እርምጃ ለመውሰድ ተብሎ የተዘጋው የደብረ ብርሀን-ደሴ ያለው የየብስ ትራንስፖርት ከተዘጋ አንድ ወር አልፎታል።