በሱዳን ተኩስ አቁም ቢታወጅም ከባድ ውጊያ እየተደረገ ይገኛል
በሱዳን ጦር እና አር.ኤስ.ኤፍ ተብሎ በሚጠራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ዛሬ 18ኛ ቀኑን ይዟል።
በሱዳን ጦር ኃይሎችእና በፈጥኖ ደራሽ ሰራዊቱ (አርኤስኤፍ) መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ካርቱም፣ አጎራባች በሆነችው ኦምዱርማን እና በሌሎችም አካባቢዎች ከባድ ውጊያ አለ።
ዛሬ ማክሰኞ በሱዳን ያለው ሁኔታ እንደሚከተለው ቀርቧል፤
የሱዳን ውጊያ
በሱዳን ጦር እና አር.ኤስ.ኤፍ ተብኮ በሚጠራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የተደረሱ የተኩስ አቁሞችን ለማራዘም ስምምነቶች የተደረሱ ቢሆንም አሁንም በካርቱምና ሌሎችም አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው።
የአየር ድብደባዎች እና የከባድ መሳሪያ ውጊያ ካርቱምን እና ሌሎችን ከተሞች እየናጠ ነው የተባለ ሲሆን፤ በርካቶችም መኖሪያቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል።
በካርቱም ህግ ወጥነት እየተራከተ ነው የተባለ ሲሆን፤ በምእራብ ዳርፉር ክልል ኤል-ጄኒና ከተማ በተከሰተ ግጭት 96 ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ሰብዓዊ ቀውስ
በሱዳን እየተካሄደ ባለው እና 18ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት 528 ሰዎች መሞታቸውን እና 4 ሸህ 600 ሰዎች መቁሰላቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ዛሬ ባወጣው መረጃ ቁጥራው 800 ሺህ የሚደርሱ ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ሊሰደዱ ይችላሉ ብሏል
ግብጽ እስካሁን 40 ሺህ ሱዳናውያንን ድንበሯን በማቋረጥ ወደ ግዛቷ መግባታቸውን አስታውቃለች።
በሀገር ውስጥም ከ330 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል የተባለ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 70 በመቶው ከምዕራብ እና ደቡብ ካርቱም የተፈናቀሉ ናቸው ተብሏል።
ዲፕሎማሲ እና የውጭ ዜጎችን ማስወጣት
የሩሲያ ጦር በአራት የጦር አውሮፕላኖች 200 ሰዎችን ከሱዳን ማውጣት መጀመሩን በዛሬው እለት ያሳወቀ ሲሆን፤ ዜጎቹን የማስወጣት ስራም ተጀምሯል።
የአሜሪካ ባህር ኃይል ጦር መርከብ 308 ሰዎችን በመጫን የሳዑዲ አረቢያ ቀይ ባህር ወደብ ምድረሷ ተነግሯል።
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ በሱዳን በጦርነት መካከል ለሚገኙ ዜጎች እርዳታ መላክ በሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸትኬንያ ናይሮቢ ደርሰዋል።