በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ አካባቢ የ15 አርሷደሮች የጤፍ ክምር ተቃጠለ
ቃጠሎው ትናንት ሌሊት የደረሰ ነው እንደ አርሶ አደሮቹ ገለጻ
የጤፍ ክምሩ 76 እንደሆነ የተቃጠለባቸው አርሷደሮች ተናግረዋል
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ ከ50 በላይ የጤፍ ክምር መቃጠሉ ተገለጸ።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ስር ባለችው የማጀቴ ንኡስ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች ከ50 በላይ የጤፍ ክምር በእሳት መቃጠሉ ተገልጿል።
የጤፍ ክምራቸው ከተቃጠለባቸው አርሶ አደሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሞገድ ረዳ ለአልአይን አማርኛ እንደተናገሩት “ የዓመት ቀለቤ በእሳት ተቃጥሎብኛል” ብለዋል።
የአጣዬው ጥቃት “በከባድ የቡድን መሣሪያ ጭምር በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ባለው የታጠቀ ኃይል የተፈጸመ ነው”- የአማራ ክልል
20 ኩንታል የሚገመት ምርት አገኝበታለሁ ብዬ የማስበው እና ክረምቱን ሙሉ የለፋሁበት ጤፌ ትናንት ሌሊት ተቃጥሎ አደር የሚሉት አርሶ አደር ሞገስ “ድርጊቱ አሳፋሪ እና እህል ከሚመገብ ፍጡር የማይጠበቅ” ነው ብለዋል።
“የጤፍ ሰብሌን በአስቸጋሪው የክረምት ወራት ስድስት ቀናት በጎርፍ እና ከዶፍ ጋር ታግዬ ያዘመርኩት ነበር በዚህ መንገድ መውደሙ ያሳዝናል” ያሉት አርሶ አደሩ “በረሀብ ሳልሞት መንግስት ይድረስልኝ” ብለዋል።
ጤፉን ማን አቃጠለው? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄም “በአጎራባች ቀበሌዎች የሚኖሩ ኦሮሞዎች ውጪ ሌላ ማንም ሊያቃጥለው አይችልም” ሲሉ አርሶ አደር ሞገስ መልሰውልናል።
የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ የመንግስት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አህመድ ሰይድ በበኩላቸው ከትናንት በስቲያ በማጀቴ ንኡስ ወረዳ ስር ባሉ ሁለት ቀበሌዎች የ15 አርሶ አደሮች የጤፍ ክምር መቃጠሉን አረጋግጠውልናል።
እንደ አቶ አህመድ ገለጻ “በአግላ ማጀቴ ቀበሌ እና አንቃር ኮበኮብ ቀበሌ ስር ያሉ የ15 አርሶአደሮች ንብረት የሆነ 425 ሺህ 500 ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው ጤፍ ተቃጥሏል።”
በአማራ ክልል አጣዬ አካባቢ በተከሰተ የጸጥታ ችግር በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ
የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የጸጥታ አመራሮች እንዲሁም በአካባቢው ያለው የአገር መከላከያ ሰራዊት እና ፌደራል ፖሊስ አመራሮች ቦታው ድረስ በመምጣት ምልከታ ማካሄዳቸውን የተናገሩት አቶ አህመድ ተጎጂ አርሶ አደሮች ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲሁም ድርጊቱን ፈጽመውታል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን መያዝ ላይ ትኩረት እንዲደረግ ውሳኔ መተላለፉንም ገልጸዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ያለው የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ፤ እንዲሁም በኦሮሚያ ብሄረሰብ ዞን ስር ያሉት ሁለት ወረዳዎች ማለትም የጨፋ ሮቢት ከተማ አስተዳድር እና የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ የጸጥታ አመራሮች፤የሰላም ኮሚቴዎች እና የአገር ሽማግሌዎች ተጎጂዎችን ለመርዳት እና ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም አቶ አህመድ ተናግረዋል።
ጉዳዩን የሚያጣራ የጋራ የምርመራ ቡድን መቋቋሙን የገለጹት አቶ አህመድ በምርመራው መሰረት ወንጀሉን የፈጸሙት ተጠርጣሪዎች የሚገኝበት ወረዳ ጤፋቸው ለተቃጠለባቸው አርሶ አደሮች ካሳ እንዲከፍል መወሰኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የህዝብ ሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኡመር መሀመድ በበኩላቸው የአርሶ አደሮቹን የጤፍ ክምር መቃጠል መስማታቸውን እና በድርጊቱ ማዘናቸውን ተናግረዋል።
“የጤፍ ክምሩን ያቃጠሉት አካባቢው እንደከዚህ ቀደሙ ወደ ጦርነት እንዲገባ በሚፈልጉ አካላት የተፈጸመ ነው” ያሉት አቶ ኡመር ወንጀሉን የፈጸሙት አካላት ከሁለቱም ብሄረሰቦች ሊሆኑ እንደሚችሉም አክለዋል።
ተጠርጣሪዎቹን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል ወንጀል መርማሪዎች ከሀይማኖት አባቶች እና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ስራ መጀመራቸውንም አቶ ኡመር አክለዋል።
አጣዬ ከተማ በታጣቂዎች ጥቃት “ሙሉ በሙሉ መውደሟ” ተገለፀ
ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጋር በሚዋሰነው በዚህ አካባቢ ከአሁን ቀደምም ከፍተኛ ውድመት የተፈጸመባቸው ጥቃቶች አጋጥመዋል፡፡ለዚህም አጣዬንና አካባቢውን ማንሳት ይቻላል፡፡
ይህን ተከትሎም አካባቢው ከሸዋሮቢት ጀምሮ እስከ ኬሚሴ ድረስ በኮማንድ ፖስት ላይ ነው፡፡