በቆቦ ግንባር ሙጃና ጥሙጋ ነጻ በማውጣት ወደ አላማጣ ከተማ እየገሰገሱ መሆኑን አስታውቋል
የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ የጸጥታ ኃይሎች አብዛኞቹን የዋግ ኅምራ አካባቢዎች ነጻ በማውጣት የዞኑን ዋና ከተማ ሰቆጣን መቆጣጠራቸውን መንግስት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ማምሻውን ባወጣው መግለጫው፤ “አካባቢው ከህወሓት ኃይሎች ነጻ በሚወጣበት ጊዜ የዋግ ኅምራ ሚሊሻዎችና የአካባቢው ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመጣመር ደጀንነቱን በብቃት አሳይቷል” ብሏል።
“የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ የጸጥታ ኃይሎች ቀሪዎቹን ሥፍራ እያጸዱ፣ የፈረጠጠውን የህወሓት ኃይል እየደመሰሱ፣ ወደ አበርገሌ በመገሥገሥ ላይ ይገኛሉ” ብሏል መግለጫው።
በተያያዘም “የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች፣ በቆቦ ግንባር በአንድ በኩል ሙጃና ጥሙጋ ላይ የሠፈረውን የህወሓት ኃይል በማስለቀቅ ወደ አላማጣ ከተማ እየገሰገሱ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተኩለሽን ተቆጣጥረው በማጽዳት፣ ወደ መረዋና ኮረም እየገሠገሡ ይገኛሉ” ብሏል።
“ከአማራ እና አፋር ክልሎች ተሸንፎ የወጣው ህወሓት በአንድ በኩል ለሰላም ሲል የወጣ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሽንፈቱ ውኃ የማይቋጥር ምክንያት እያቀረበ፣ አድኑኝ የሚል እሪታ እያሰማ፣ በለመደው ውሸት የትግራይን ሕዝብና የዓለምን ማኅበረሰብ ለማደናገር እየሞከረ ይገኛል” ብሏል መንግስት በመግለጫው።