መንግስት ከህወሓት ጋር ሊደራደር ነው የሚባለው መረጃ ሀሰት ነው - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
መንግስት አሁንም ከሽብርተኛ ቡድን ጋር በይፋ እደራደራለሁ አላለም ብለዋል
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር መተማመን የሞላበት ግንኙነት መመስረት እንደመትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር መወያየታቸውን አስታውቀዋል።
“ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ከህወሀት ሀይሎች ጋር በጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ምክንያት ግንኙነታቸው ወደ መጠራጠር ገብቷል” ብለዋል አምባሳደር ዲና።
ይሁንና አሁን ላይ አሜሪካ የኢትዮጵያን ፍላጎት መረዳት መጀመሯን የተናገሩት አምባሳደር ዲና፤ ውይይቶች በመቀጠላቸው ግንኙነቱ በመሻሻል ላይ መሆኑንም አክለዋል።
መልዕክተኞቹ በውይይቱ ወቅት "አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር መጠራጠር የሌለበት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበራቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነት መመለስ ትፈልጋለች" ሲሉ መናገራቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የነበራትን ሽብርተኝነትን መዋጋት እና ሰላም ጥበቃ ዋነኛዋ ሀገር እንድትሆን የአሜሪካ ፍላጎት መሆኑንም መልዕክተኞቹ መናገራቸው ተገልጿል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት በፊት ወደ ነበሩባቸው ጊዜያት እንዲመለሱ የሁለቱም ሀገራት ፍላጎት መሆኑንም አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ተናግረዋል።
ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከዳያስፖራዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ መንግስት ከህወሀት ጋር ድርድር ያደርጋል ብለዋል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ " መንግስት እስካሁን ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር እንደሚደራደር አላሳወቀም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
መንግስት ህወሓትን አሁንም ቢሆን በሽብርተኝነት ነው የሚመለከተው ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ድርድር ሊደረግ ነው የሚለው መረጃ ትክክል አለመሆኑን እና ከመንግስት በኩል የወጣ አለመሆኑንም ገልፀዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ እና በጦርነቱ ምክንያቶች ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የ700 ሺህ ቶን ምግብ እና ምግብ ነክ እርዳታ እንደሚሰጥ ባሳለፍነው ሳምንት ከድርጅቱ መሪ ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ተናግሯልም ተብሏል።
ከሰሞኑ የአምባሳደሮች ሹመት ባለፉት ሶስት ዓመታት በዲፕሎማሲ መስክ የኢትዮጵያን ፍላጎት ባስጠበቀ መንገድ እንደ አዲስ ለማደራጀት የተጀመረው ጥረት አንዱ አካል መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
የአምባሳደርነት ሹመቱ ሙያን እና አቅምን መሰረት ባደረገ መንገድ የተደረገ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፤ አምባሳደሮቹ የተመደቡባቸው ሀገራት በቀጣይ ይፋ ይደረጋልም ብለዋል።
በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ህይወታቸውን በመምራት ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ከእስር ለማስለቀቅ ዓላማው ያደረገ ልዑክ ወደ ሪያድ ማቅናታቸው ተገልጿል።
የልዑክ ቡድኑ አባላት በሪያድ ቆይታቸው ከሳውዲ መንግስት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንደሚወያዩ እና በችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ይረዳሉ ተብሏል።