አሜሪካንን ጨምሮ 16 ሀገራት በኢትዮጵያ የተካሄደውን ጥምር ምርመራ ሪፖርት እንደሚቀበሉት ተናገሩ
ሀገራቱ ኢሰመኮ እና የተመድ የተመድ የሰብዓዊ መብት ቢሮ የምርመራ ሪፖርት ግኝቶች እንዲተገበሩ ግፊት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል
የኢትዮጵያ መንግስት የግጭቱ ሰለባዎችን ለመርዳት እያደረገ ላለው ጥረት እውቅና እንደሚሰጡም ሀገራቱ አስታውቀዋል
አሜሪካንን ጨምሮ 16 የዓለማችን አገራት በኢትዮጵያ የተካሄደውን ጥምር ምርመራ ሪፖርት እንደሚቀበሉት ተናገሩ፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ ግጭት ዙሪያ ያደረጉትን የጋራ ሪፖርት ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
- የትግራይ ግጭት ተሳታፊዎች “በተለያየ መጠን” የሰብአዊ መብቶችን መጣሳቸውን የምርመራ ቡድኑ ገለፀ
- የኢትዮጵያ መንግስት በምርመራ ሪፖርቱ የተወሰኑ ይዘቶች ላይ ትልቅ ቅሬታ እንዳለው ገለጸ
አሜሪካን ጨምሮ 16 የዓለማችን ሀገራት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የተካሄደውን ጥምር ምርመራ ሪፖርት እንደሚቀበሉት በጋራ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል።
አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አይስላንድ፣ አየርላንድ፣ ሉግዘንበርግ፣ኔዘርላንድ፣ ኒውዝላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን እና እንግሊዝ በጣምራ ሪፖርቱ ላይ የጋራ መግለጫ ያወጡ ሀገራት ናቸው።
ሀገራቱ በመግለጫቸው ሁለቱ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቋማት በትግራይ ክልል ባለው ጦርነት ዙሪያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ያወጡት ሪፖርት ገለልተኛ እና ተጠያቂነትን ሊያሰፍን የሚችል መሆኑን አስታውቀዋል።
የጋራ ሪፖርቱ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን ከማስፈን ባለፈ ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ እየተበራከቱ በመጡ ጥቃቶች ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ በር የሚከፍት መሆኑንም ሀገራቱ በጋራ መግለጫቸው ጠቁመዋል።
በዚህ ሪፖርት መሰረት በጥቃቱ ሁሉም አካላት ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የህወሓት ታጣቂዎች፣የኤርትራ ሰራዊት እና በህወሃት የተደራጁት ሳምረ የተሰኘው የወጣቶች ቡድን መሳተፋቸው በሪፖርቱ በመረጋገጡ ሁሉም ተሳታፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ሀገራቱ አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ ላይ የተሳተፉ ሁሉም አካላት በሪፖርቱ ግኝቶች መሰረት ወደ መፍትሄ እንዲመጡም አክለዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን እነዚህ 16 አገራት የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነቱ ለተጎዱ አካላት እያደረገ ያለው ድጋፍ፣ ወንጀል ፈፅመዋል በሚል በተጠረጠሩ አካላት ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ምርመራ መጀመሩ እና እያደረጋቸው ላለው ሌሎች ጥረቶች እውቅና እንደሚሰጡ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
መንግስት የጀመረውን ጥረት እንዲቀጥልበት የጠየቁት እነዚህ ሀገራት፤ በተለይም ለተጎጂዎች ተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ድጋፎች እንዲደርሱ፣በወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ተጨማሪ ምርመራዎች እንዲካሄዱ እና ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም ብሄራዊ ውይይት እንዲያካሂድም አሳስበዋል።
ኤርትራ፤ የትግራይ ግጭትን በተመለከተ የኢሰመኮ እና የተመድን የጋራ ሪፖርት እንደማትቀበል አስታወቀች
ሀገራቱ ከዚህ ባለፈ ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እና መረጋጋቷ እንድትመለስ ድጋፍ እንደሚያደርጉና የግዛት አንድነቷን እንደሚያከብሩ በመግለጫቸው አሳውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በትግራይ ግጭት ዙሪያ ያደረጉትን የጋራ ምርመራ ሪፖርት ባሳለፍነው ረቡዕ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በሪፖርታቸውም በግጭቱ ተሳታፊ አካላት መጠኑ ቢለያይም የሰብአዊ መብት እና ዓለም አቀፍ የስደተኞች መብት ጥሰቶችን ጨምሮ እስከ ጦር ወንጀል ሊደርሱ የሚችሉ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን አስታውቀዋል።
በትግራዩ ግጭት ዘር የማጥፋት ወንጀል (ጄኖሳይድ) መፈጸሙን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች አለመገኘታቸው መግለፃቸው ይታወሳል።