“በኢትዮጵያ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ሁኔታ የለም”- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው” ብለዋል
አምባሳደር ሬድዋን “አፍሪከ ህብረት የሰላም ድርድሩ የሚካሄድበት ቀን እስኪያሳውቅ እየጠበቅን ነው” ብለዋል
በኢትዮጵያ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ሁኔታ የለም ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያን በተመለከተ ትናንት ምሽት በሰጡት መግለጫ “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
“አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ወታደራዊ መፍትሄ የለውም” ያሉት ዋና ጻሃፊው፤ በትግራይ ክልል ያለው ግጭት አሁኑኑ ማብቃት አለበት” ብለዋል።
ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትዊተር ገጻቸው፤ “የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሌላ መልክ ለመቀባት ለሚፈልጉት አካላት በኢትዮጵያ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ነገር የለም” ብለዋል።
“ግጭቱ ክጥጥር ውጪ ሆኖ የነበረው ወደ ሌሎች ክልሎች በተስፋፋበት ጊዜ ነበር” ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፤ አሁን ሁሉም ነገር በታቀደው መሰረት እየሄደ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
አምባሳደር ሬድዋን አክለውም ለሚካሄደው የሰላም ድርድር “አፍሪከ ህብረት የሰላም ድርድሩ የሚከሄድበት ቀን እስኪያሳውቅ እየጠበቅን ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ትናንት ባወጣው መግለጫ ለሰላም ቁርጠኛ መሆኑን ገልጾ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማረጋገጥ በትግራይ ክልል የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችን እና የፌደራል ተቋማትን እንደሚቆጣጠር ማሳወቁ ይታወሳል።
በዛሬው እለትም መንግስት ባወጣው መግላጫ፤ የመከላከያ ሰራዊት ሽሬ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞችን መቆጣጠሩን እና በቅርቡ የሰብዓዊ ድጋፎች እና የተቋረጡ መሰረታዊ አልግሎቶችን ለማስጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል።