“የገንዘብ እጥረት አለብን” በሚል የተሟላ የባንክ አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ የተሟላ የባንክ አገልግሎት እንዲጀመር ውሳኔ ማሳለፋቸውን መንግስት ገልጿል
ነዋሪዎቹ፤ በአካውንታችን ያለውን ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንድንችል መንግስት ኃላፊነቱን ይወጣ ሲሉ ጠይቀዋል
በመንግስት እና ህወሓት መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሶስት ወር ሆኖታል፡፡ በስምምነቱ መሰረት በትግራይ ክልል የመሰረታዊ አግልገሎቶች መመለስ የሚለው አንዱ ሲሆን ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸው ይገለጻል፡፡
አሁን ላይ እንደ ቴሌኮም ፣ ኤሌክትሪክ እና የአየር ትራንስፖርት ከመሳሰሉ አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ተስፋ ሰጪ አፈጻጸሞች ቢሰተዋሉም የባንክ አገልግሎቱ በታሰበው ልክ እንዳልሆነ ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
አል-ዐይን አማርኛ ያናገራቸው የሽሬ፣አክሱም፣ አዲግራት እና መቀሌ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ባንኮቹ የገንዘብ ፍሰት አቅርቦት ችግር ስላለባቸው ተገቢውንና የተሟላ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፡፡
የሽሬ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኪዳማርያም ሃይሉ በሽሬ እና አከባቢዋ ንግድ ባንክ እና የግል ባንኮች አገልግሎት መሰጠት መጀመራቸውን ገልጸው፤ ይሁን እንጅ ንግድ ባንክ ከሃዋላ ውጭ ሌላ አገልግሎት እንደማይሰጥ እንዲሁም የግል ባንኮቹ የገንዘብ እጥረት አለብን በሚል ከ1ሺህ በላይ ብር እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡
የአክሱም ነዋሪው አቶ አሸናፊ ካሕሳይ በበኩላቸው በከተማዋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዳሽን፣አንባሳ እና ወጋገን ባንኮች በተወሰነ መልኩ አግልግሎት መስጠት ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ “የገንዘብ እጥረት አለብን” በሚል አገልግሎት አስከማቋረጥ ደርሷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ አሸናፊ ኪዘህ በፊት ንግድ ባንክ የሃዋላ አገልግሎት (አስከ 10 ሺህ ብር) እንዲሁም ሌሎች የግል ባንኮቹ የተለያየ የብር መጠን (ከ1 ሺህ እነስከ 5 ሺህ) ሲሰጡ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ብንሄድም ብር የለንም የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡን ብለዋል፡፡
ተመሳሳይ ችግር እንዳለ የምትናገረው ሌላኛዋ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወጣት ብርክቲ ገሰሰ በበኩሏ በመቀሌ አሁንም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመረ ገልጻለች፡፡
ወጣት ብርክቲ የግል ባንኮቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ፍሰት አቅርቦት ችግር በመኖሩ ሰዎች ብራቸውን እንኳን መጠቀም እንዳልቻሉ ተናግራለች፡፡
“አንዱ ጓደኛዬ በቅርቡ በአቢሲኒያ ባንክ 60ሺህ ብር በሃዋላ ተልኮለት የተሰጠው ግን 2ሺህ ብር ብቻ ነው” ያለችው ብርክቲ ባንኮች የሚሰጡት ብር መሰረታዊ ሸቀጦች እንኳን ለመግዛት የማያስችል ነው ብላለች፡፡
“በበዓል ቀን ደሮ 1ሺህ 600 ብር በገባበት ወቅት፤ ከባንክ 1ሺህ ወይም 2 ሺህ ብር ብቻ መቀበል ምን ማለት ነው…?” ስትልም ትጠይቃለች ብርክቲ፡፡
“ከበቂ በላይ ተሰቃይተናል፤ ይበቃናል” የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ በአካውንታቸው ያለውን ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንዲችሉ የፌዴራል መንግስትም ሆነ የክልሉ መንግስት የሰላም ስምምነቱን በመተግበር ኃላፊነታቸው እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
የነዋሪዎቹን ጥያቄ መነሻ በማድረግ አል-ዐይን አማርኛ ያነገራቸው የወጋገን ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ሃፍቶም ገብረእግዝአብሄር ፤ ደንበኞቹ የሚያነሱት ችግር (የገንዘብ እጥረት) ትክክል መሆኑን አምነው ችግሩን ለመፍታት በወጋገን ባንክ በኩል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎት ከጀመርን ወር ከአንድ ሳምንት ሆኖናል የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ እስካሁን ከኤሌክትሮኒክ ባንኪንግ(የሞባይል እና ኤቲኤም አገልግሎት) ውጭ ሁሉም አይነት አገልግሎት እየሰጠን ነው ብለዋል፡፡
“ 70 ያህሉ ቅርንጫፎቻችን አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ ከአላማጣ እስከ አዲግራት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጠን ነው፡፡ ኔትዎርክ በሌለባቸው ካልሆነ በስተቀረ፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ ባላንስ ትራንዛክሽኖች በሙሉ ተስተካክለው ደንበኛ ከነበረው ባላንስ እየከፈልን ነው” ሲሉም ነው የተናገሩት ስራ አስኪያጁ፡፡
ደንበኞች የሚያወጡት ገንዘብ ለሁሉም ለማዳረስ በሚል የሚሰጠው የገንዘብ መጠን እንደየ ቅርንጫፎቹ እንደሚወሰን የገለጹት አቶ ሃፍቶም፤ እሰካሁን ባለው አሰራር ከ1ሺህ እስከ 5ሺህ ብር ሲሰጥ መቆየቱም ገልጸዋል፡፡
የደንበኛን ፍላጎት እያሻሻሉ ለመሄድ በሂደት በርካታ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው የገለጹት የዲስተሪክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሃፍቶም ገብረእግዝአብሄር፤ በቅረቡ ከዋና ባንክ 50 ሚሊዮን ብር ተልኮ እንደነበር በአብነት በማንሳት፡፡
ያለው የገንዘብ እጥረት በቀጣይ ቀናት ሙሉ በሙሉ ይቀረፋል የሚል ተስፋ እንዳለቸውም ጭምር ተናግረዋል ስራ አስኪያጁ፡፡
አበባ በሚል ስም መጠራት የፈለገችው ሌላኛዋ የአንባሳ ባንክ ባለሙያ በበኩሏ ነዋሪዎቹ የሚያነሱት ጥያቄ ተገቢ መሆኑ ለአል-ዐይን አማርኛ አረጋግጣለች፡፡
“ከዚህ ቀደም በሳምንት አንዳንዴም በሁለት ሳምንት 2ሺህ በወር 4ሺህ ብር እንሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ገንዘብ ስሌለለን አግልገሎት መስጠት አቁመናል፤ ካቆምን ወር ሊሆነን ነው” ስትልም ነው የተናገረችው ወ/ሪት አበባ፡፡
ባንኮቹ ከሂሳብ ገንዘብ ማውጣትን ጨምሮ ተሟላ አግልገሎት መስጠት የሚጀምሩት የኦዲት (ሂሳብ) ስራ ካጠናቀቁ በኋላ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡
ከአንድ ወር በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቢ ሳኖ ለመገናኛ ብዚሃን ሲናገሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመቀሌ ዲስትሪክት ጋር ተገናኝቶ ትክክለኛ ኦዲት ስራ ከተከናወነ በኋላ ደንበኞች ገንዘብ ማውጣት እንደሚፈቀድላቸው ገልጸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በሰላም ሚኒሰቴር የሚመራው የትግራይ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ማስተባበሪያም እንዲሁ የኦዲት ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ ወደ ስራ እንደሚገባ ሲገልጽ ነበር፤ ምንም እንኳን የኦዲት ስራው ተጠናቋል ከተባለ በኋላም ቢሆን ወደ ስራ ባይገባም፡፡
በትግራይ የተሟላ የባንክ አገልግሎት መጀመር ለሁለት አመት የባንክ አገልግሎት ሳያገኝ ለቆየው የክልሉ ነዋሪ ትልቅ ነገር እንደሆነ ይታመናል፡፡
በተለይም ለሁለት አመት ገደማ በአካውንቱ ያለውን ገንዘብ መጠቀም ላልቻለው ከ100 ሺህ በላይ የሚገመተው የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትናንትናው እለት ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ከህወሓት ተደራዳሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በትግራይ ያለው የባንክ አገልግሎት በተሟላ መልክ እንዲሰጥ ውሳኔ ማሳለፈፋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን በትዊትር ገጻቸው አስታውቋል።