በስምምነቱ አተገባበር ጉዳይ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መወያየታቸው ተገለጸ
የፕሪቶሪያው ስምምነት ህወሓት ትጥቅ ለመፍታት ተስማምቷል
በኬንያ የፌደራል መንግስት እና የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማስፈጸሚያ እቅድ ላይ ተፈራርመዋል
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ካደረጉት የዘላቂ ግጭት ማቆም ስምምነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር መወያየታቸው የአሜሪካ ኢምባሲ በኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡
ኢምባሲው እንደገለጸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልል እርዳታ ለማድረስ እና መሰረታዊ አገልግሎት ለማድረስ እያደገ ላለው ጥረት እውቅና እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ብሊንከን ሁሉም የውጭ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ እና በተመሳሳይ ጊዜ የህወሓት ሃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረግን ጨምሮ የዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን በወይይቱ ማንሳታቸውን ገልጿል ኢምባሲው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር አድርገውታል ስለተባለው ወይይት ያለው ነገር የለም፡፡
በአፍሪካ ህብረት መሪነት የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በፕሪቶሪያ የዘላቂ ግጭት ማቆም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በኬንያ የስምምነት ማስፈጸሚያ እቅድ ላይ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡
በኬንያ የፌደራል መንግስት እና የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማስፈጸሚያ እቅድ ላይ ተፈራርመዋል፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት ህወሓት ትጥቅ እንዲፈታ፣ የሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ፣ የፌደራል መንግስት በትግራይ ያሉ የፌደራል ተቋማትን እንዲቆጣጠር እና ጊዜያዊ የክልል አስተዳደር እንዲዋቀር የሚሉ አንቀጾች ይገኙበታል፡፡