ህወሓት በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ መክፈቱን መንግስት ገለፀ
የህወሓትን ወረራ የመከላከያ ሠራዊት እየተከላከለ መሆኑን አስታውቋል
መንግስት ለሰላም የተዘረጋው እጅ እንዳይታጠፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚቻለውን እንዲያደርግ አሳስቧል
ህወሓት በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ መክፈቱን መንግስት አስታውቋል።
የኢትዮጵያ የመንግስት የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ “ህወሓት በምሥራቅ አማራ በኩል በቆቦና አካባቢው የከፈተው ወረራ የመከላከያ ሠራዊትና በደጀን ሕዝብ የመከላከል ብቃት ባሰበው ልክ አልሄደለትም” ብሏል።
- የፌደራል መንግስትና ህወሓት ባወጡት መግልጫ ጦርነት መጀመሩን አስታወቁ
- የመከላከያ ሠራዊት የጦር መሳሪያ ጭኖ የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሶ የገባ አውሮፕላን “መትቼ ጣልኩ” አለ
“በዚህም ምክንያት ለሰላም የተሰጠውን ሁለንተናዊ አማራጭ አሽቀንጥሮ ጥሎ ወረራውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እያስፋፋ ይገኛል” ሲልም መንግስት በመግለጫው አስታውቋል።
“ህወሓት በዋግ፣ በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ ከፍቷል” ያለው መግለጫው፤ ይሄንን ወረራ የመከላከያ ሠራዊት በተሟላ ዝግጅትና በጽኑ ቁመና እየተከላከለ ይገኛል” ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት “አሁንም ለሰላም አማራጮች የዘረጋቸውን እጆች ዛሬም ድረስ አላጠፈም” ሲልም መግለጫው አስታውቋል።
“ለሰላም የተዘረጋው እጅ በህወሓት ዕብሪታዊ ወረራ ምክንያት እንዳይታጠፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚቻለውን እንዲያደርግ” የኢትዮጵያ መንግሥት አሳስቧል።
“የትግራይ ህዝብም ይሄንን ወረራ በማውገዝ ህወሓት ከሚያስከትልበት መከራ ራሱን ነጻ ያውጣ” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ለወራት ቆሞ የነበረውን ጦርነት መጀመሩን ባወጡት ባሳለፍነው ረቡዕ ነሃሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ህወሓት ባወጣው መግለጫ መከላከያ ሰራዊትና እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኃይሎች ትግራይ ደቡባዊ አቅጣጫ ባለው ግንባር በኩል ተኩስ መክፈታቸውን አስታውቋል።
የህወሓት መግለጫን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በዛሬው እለት ጠዋት 11 ሰዓት በተያየ አቅጣጫ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል።
የፌደራል መንግስት በሽብርተኝነት ከፈረጀው ህወሓት ጋር ያለውን ግጭት በድርድር ለመፍታት ማስታወቁ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚደረደር መግለጹ ይታወሳል። ህወሓትም በተመሳሳይ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነበር።