ህወሓት የአፍሪካ ሕብረት "ሰላም ሊያመጣ አይችልም" አለ
ህወሓት ከዚህ ቀደም ኦባሳንጆ የሚያመቻቹት ነገር ፍትሀዊ ውጤት ይኖረዋል ብሎ እንደማያምን ገልጾ ነበር
የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር የሚደረገው ድርድር የሚመራው በአፍሪካ ሕብረት ብቻ እንደሆነ ገልጿል
የትግራይ ክልል እያስተዳረ የሚገኘው እና በህዝብ ተወካዮች መክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት፤ የአፍሪካ ሕብረት በትግራይ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ "አያመጣም" ሲል ተቸ።
የኢትዮጵያ መንግስት በሕግ የሚፈልጋቸው የቡድኑ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ የአፍሪካ ሕብረት ለሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሰላም ሊያመጣ እንደማይችል ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ አፍሪካ ሪፖርት በተሰኘው መጽሄት ላይ የቡድናቸውን አቋም ጽፈዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አሁን ላይ ያለውን ሁኔታ እንዳልተገነዘቡት አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
አሁን ካለው ሁኔታ ይልቅ ኦባሳንጆ በአፍሪካ ቀንድ የህብረቱ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው የተሾሙበት ወቅት የተሻለ ነበርም ብለዋል አቶ ጌታቸው።
ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ መንግስትና ህወሃት ያደርጉታል በተባለው ድርድር የኤርትራ መንግሥትን ለመጋበዝ ማሰባቸው ትክክል እንዳልሆነም ጌታቸው ረዳ ጽፈዋል።
ኦባሳንጆ የሰላም ንግግሩን ሂደት በተመለከተ ለህብረቱ የፖለቲካ፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽን በሰጡት ማብራሪያ ኤርትራም መሳተፍ አለባት የሚል ፍንጭ መስጠታቸው ይታወሳል።
ከፍተኛ ተወካዩ ይህንን ከተናገሩ በኋላ ህወሓት ተቃውሞውን ገልጿል። የቡድኑ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ቀደም ሲል በክልሉ ለሚገኙ መገናኛ ብዙሃ በሰጡት መግለጫ፤ ኦባሳንጆ የሚያመቻቹት ነገር ፍትሀዊ ውጤት ሊያመጣ አይችልም ብለው ነበር። አሁን ደግሞ ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ህብረትም ሰላም አያመጣም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሓት ጋር የሚደራደር ቡድን ሰይሞ ስራ ማስጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፤ ከህወሓት ጋር የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ህብረት ስር መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል።
ከህወሓት ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ ላይ የአፍሪካ ህብረትን አቋም የሚደግፉ ታዋቂ አፍሪካዊያን ቢሳተፉ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞ እንደሌለው ገልጾ ነበር።
ነገር ግን ከህወሃት ጋር ይደረጋል የተባለው ንግግር የሚመራው በአፍሪካ ሕብረት ብቻ እንደሆነ የፌደራል ምንግስት መግለጹ ይታወሳል።
የመንግስት ተደራዳሪ ቡድን መሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስታቸው ችግሩን በሰላም ለመፍታት ፍላጎት እንዳለው ትናንትና በሰቆጣ ከተማ ተናግረዋል።
ይሁንና ህወሃት ከያዛቸው አካባቢዎች ለቆ መውጣት አለበት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ከወጣቶች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ሶስት አመት ከመዋጋት 10 ዓመት መነጋገር ይሻላል ብለዋል።