ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ የሚገኝው ህወሓት እነ ጌታቸው ረዳን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አነሳ
ፓርቲው የተነሱት የማዕከላዊ አባላት በተራ አባልነት ከመቀጠል ውጪ በህወሓት ስም ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም ብሏል
በፓርቲው ዋና ሰዎች መከፋፈል መፈጠሩን ተከትሎ በክልሉ ውጥረት እንዲባባስ አድርጓል
ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ የሚገኝው ህወሓት እነ ጌታቸው ረዳን ካማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አነሳ።
በአመራሮች መካከል ክፍፍል ያጋጠመው ህዝባዊ ሀርነት ትግራይ (ህውሓት) እያካሄደ በሚገኝው ጠቅላላ ጉባኤ አንሳተፍም ያሉ አባላቶችን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ማንሳቱን አስታውቋል።
ፓርቲው ባወጣው መግለጫ" የተለየ ሃሳብ አለኝ "የሚል በጉባኤ ያልተገኘ አካል ወደ ጉባኤው ቀርቦ ሃሳቡን በነፃነት እንዲገልፅ ፣ በዴሞክራሲያዊ ሙግት ለሚተላለፉት ውሳኔዎች ተገዢ" እንዲሆን ነሃሴ 8/2016 ዓ.ም ጥሪ ማቅረቡን አስታውሷል።
በዚህም የድርጅቱ ጉባኤ ከተሰየመበትና ከተጀመረበት ነሀሴ 7/2016 ዓ.ም ቀን በኋላ ያልተሳተፉ አመራሮች የተራ አባል እንጂ የማእከላዊ ኮሚቴ የሚባል ሃላፊነት የላቸውም ብሏል፡፡
ስለሆነም ከህግና ተቋማዊ የደርጅቱ አሰራር ውጪ በአሁኑ ወቅት በህወሓት ስም ማንኛውም የፓለቲካ ስራ ለመፈፀም ሃላፊነት ያለው የማዕከላዊ ኮሚቴና የማእከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን ሆነ ሌላ አካል የለም ሲል ውሳኔውን አስታውቋል፡፡
ህውሓት የቁጥጥር ኮሚሽን እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሲል የገለጻቸው በጉባኤው ላይ እንደማይሳተፉ አቋማቸውን የገለጹ፤ የድርጅቱን ምክትል ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች ተወካዮችን ነው፡፡
በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረትም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ በ13ኛው ጉባኤ እንደተመረጡ እና አሁን እየተካሄደ ባለው ጉባኤ የሥልጣን ዘመናቸው እንደሚጠናቀቅ ፓርቲው በዛሬው መግለጫ አስታውቋል።
ከሰሞኑ በፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት መመለስ እና ድርጅታዊ ጉባኤን በማካሄድ ዙሪያ በድርጅቱ ዋና ሰዎች መከፋፈል መፈጠሩን ተከትሎ በክልሉ ውጥረት እንዲባባስ አድርጓል።
በድርጅቱ ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን ፓርቲው ከምርጫ ቦርድ እንዲመለስለት የጠየቀው ህጋዊ ሰውነት ሙሉ ለሙሉ ምላሽ ባያገኝም ድርጅታዊ ጉባኤውን ከማካሄድ ወደ ኋላ አላለም።
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ድግሞ ጉባኤው እየተካሄደ ያለበት ሂደት፣ በፓርቲው ህጋዊ ስውነት ማስመለስ ዙርያ በቀረቡ ሰነዶች እና ሂደቶች ላይ ቅሬታ አለን በማለት ከጉባኤው እራሳቸውን አግልለዋል።
አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 14 የሚሆኑ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ፓርቲው ከሚያካሂደው ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን ይፋ ያደረጉት ባለፈው እሁድ እለት ባወጡት የጋራ መግለጫ ነበር።
ባሳለፍነው ማክሰኞ ድርጅቱ ጉባኤውን ማካሄድ መጀመሩን ተከትሎ ህወሓት በማካሄድ ላይ የሚገኝው ጉባኤ ትግራይን እና ህዝቡን ወደ አደጋ ከመክተት የዘለለ እርባና እንደሌለው ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የህውኃትን ጉባኤ አስመለክቶ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ህወሓት የቦርዱን ማሳሰቢያ ወደ ጎን በመተው ጉባኤውን ካደረገ፣ ለጉባኤው እና በጉባኤ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች እውቅና እንደማይሰጥ አሳስቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡