በህወሓት ስም አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት የቀረበውን ጥያቄ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የምርጫ ጉዳይ ክርክር ችሎት በምርጫ ቦርድና እነ’ገ/ሚካኤል ተስፋዬ መካከል የተደረገው ክርክር ውሣኔ አግኝቷል
በህወሓት ስም የሚጠራ ለረጅም ዓመታት የሚታወቅ ፓርቲ የነበረ በመሆኑ በዚሁ ስም አዲስ ፓርቲ ማቋቋም መራጩን ያደናግራል ተብሏል
በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስም አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት የቀረበውን ውሳኔ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕ.ወ.ሓ.ት) ስም ክልላዊ ፓርቲ ለመመሥረት የቀረበለትን የቅድመ ዕውቅና ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ያቀና ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በእነ’ገ/ሚካኤል ተስፋዬ መካከል ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የምርጫ ጉዳይ ክርክር ችሎት የተደረገው ክርክር ውሣኔ ማግኘቱን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
በዚህም ፍርድ ቤቱ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተብሎ የሚጠራ ክልላዊ ፓርቲ ለመመሥረት የቅድመ ዕውቅና ፍቃድ መጠየቃቸው፤ በተጠቀሰው ስያሜ የሚጠራ ለረጅም ዓመታት የሚታወቅ ፓርቲ የነበረ በመሆኑ በዚሁ ስም አዲስ ፓርቲ ማቋቋም መራጩን የሚያደናግር በመሆኑ፤ ቦርዱ ህወሓት ተብሎ የሚጠራ ክልላዊ ፓርቲ ለመመሥረት የቀረበውን የቅድመ ዕውቅና ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ስሕተት አይደለም በሚል የቦርዱን ውሣኔ በማጽናት ውሣኔ ሰጥቷል።
እነ’ገ/ሚካኤል ተስፋዬ ሌሎች ሶስት ግለሰቦች 120 መስራች አባላት ዝርዝርን በማያያዝ ግንቦት 21 2015 ዓ.ም ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስም አዲስ ፓርቲ ለማቋቋም ከምርጫ ቦርድ የጊዜያዊ ፈቃድ ጥያቄ አቅርበው ነበር።
የምርጫ ቦርድም ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም በሰጠው ምላሽ ወሓት ተብሎ የሚጠራ ክልላዊ ፓርቲ ለመመሥረት የቀረበውን የቅድመ ዕውቅና ጥያቄ አልቀበለውም በማለት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የምርጫ ጉዳይ ክርክር ችሎት ይህንኑ የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ስህተት የለበትም በሚል አጽንቶታል።