መንግስት ከህወሓት ጋር ለመነጋገር የሚያስችል ኮሚቴ ማቋቋሙን መግለጹ ይታወሳል
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የትግራይ ሕዝበ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡
ቡድኑ በሕዝበ ውሳኔ፣ በትጥቅ መፍታት እና በሌሎችም የማይነኩ ናቸው ባላቸው ጉዳዮች ላይ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ለድርድር እንደማይቀመጥ ገልጿል፡፡
በሽብርተኝነት የተፈረጀውና ከፌዴራል መንግስቱ ጋር መደራደሩ እንደማይቀር ከሰሞኑ ፍንጭ የሰጠው ህወሓት አምስት ጉዳዮችን ነው የማይነኩ ሲል ያስቀመጠው፡፡
የቡድኑ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ እና የቀድሞው የመቀሌ ዩኒቨርሲተ ፕሬዝዳንት ክንድያ ገብረ ህይወት ህይወት (ፕ/ር) ሕዝበ ውሳኔ ማድረግን የሚለውን ጨምሮ በአምስት ጉዳዮች ላይ እንደማይደራደር ገልጸዋል፡፡
ፕ/ር ክንድያ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው እንዳሰፈሩት መረጃ ከሆነ ህወሓት በ”ሁሉም የትግራይ ግዛቶች፣ በሕዝበ ውሳኔ፣ በትግራይ ሰራዊት፣ በተጠያቂነት እና በካሳ” ጉዳዮች ላይ አይደራደርም፡፡
ሌላኛው የህወሓት ተወካይ አምባሳደር ፍስሃ አስገዶምም በተመሳሳይ መልኩ ቡድኑ የማይደራደርባቸው ቀይ መስመሮች እንዳሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ግዛት ከጦርነቱ በፊት ወደነበረው መመለስ እንዳለበትና ሕዝቡ ውሳኔ ሕዝብ ማድረግ የሚፈልግ በመሆኑ በነዚህ ላይ ለመደራደር እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡
ተወካዩ፤ የህወሓት አመራሮች “የትግራይ ሰራዊት” እያሉ የሚጠሩትና የክልሉን የልዩ ኃይል አባላት አካቶ በአዲስ መልክ የተደራጀው ወታደራዊ ቡድን ትጥቅ እንደማፈታም ነው የተናገሩት፡፡
በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ሰራዊት በትግራይ ሕዝብ ላይ “የዘር ማጥፋት” ወንጀል እንደተፈጸመ ያነሱት አምባሳደሩ ተጠያቂ የሚደረግ አካል ከሌለ እንደማይደራደሩም ተናግረዋል፡፡
ህወሓት እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጡ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው እርቅና ንግግር እንቅፋት ሊሆን አይችልም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ተዋካዩ ጥሩ የመሆን ያለመሆን ጉዳይ አይደለም ሲሉ መልሰዋል፡፡
አሁን ላይ በትግራይ ላይ አለ ያሉትን “ከበባ” በወታደራዊም ሆነ በሰላማዊ መንገድ እንደሚያስከፍቱም ነው የገለጹት፡፡
ፕ/ር ክንደያ እና አምባሳደር ፍስሃ ቡድናቸው በአምስት ጉዳዮች ላይ እንደማይደራደር ከመግለጻቸው በፊት ህወሓት ከመንግስት ጋር የሚደራደር ልዑክ ለመላክ ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ከህወሓት ጋር ለመነጋገር የሚሆንና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ መዋቀሩን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ማክሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2014 ዓ/ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ከህወሓት ጋር ለመደራደር ኮሚቴ ተቋቁሞ አስፈላጊ ሁኔታዎችን እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) መንግስት ከህወሃት ጋር እንደሚያደርገው በሚጠበቀው ድርድር የአማራ ክልል እና የኤርትራ መንግስት ማወቅና መሳተፍ እንዳለባቸው የጠየቁ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት የአማራ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም ጠላት እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡