ቦሪስ ጆንሰን ከሁለት ወር በፊት ስልጣን ተገደው እንዲለቁ መደረጉ ይታወሳል
ብሪታንያ ነገ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሾማለች።
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ከፓርቲያቸው እና ከስራ ባልደረቦቻቸው በደረሰባቸው ጫና ምክንያት የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ይታወሳል።
ይሄንን ተከትሎም ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት 11 እጩዎች ቀርበው በመጨረሻም የህንድ ዝርያ ያላቸው ሪሺ ሱናክ እና ሊዝ ትሩስ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል።
ብሪታንያን ለመምራት በምርጫ ያሸነፈው ወግ አጥባቂው ፓርቲ ከሁለቱ እጩዎች መካከል በመምረጥ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ እንደሚመርጥ ተገልጿል።
እስካሁን በተሰበሰበው የህዝብ አስተያየት ሊዝ ትሩስ ቀዳሚ የብሪታንያውያን ተመራጭ ስትሆን በተለይም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ላይ የተናገሯቸው ሀሳቦች ተቀናቃኛቸውን ሪሲ ሱናክን እንደሚያሸንፉ ተገምቷል።
እጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩስ የግብር ቅነሳ እንደሚያደርጉ፣ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በኑሮ ውድነት ለተጎዱ ዝቅተኛው ማህበረሰብ የቀጥታ እርዳታ ገንዘብ እንደሚሰጡ፣ የቦንድ ሽያጭ በማድረግ ከሌሎች አቻ መገበያያ ገንዘቦች ጋር እየቀነሰ ያለው የፓውንድ ስተርሊንግ አቅምን ለማሳደግ እና ሌሎችንም ማሻሻያዎች እንደሚያደርጉ ትሩሰ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት መናገራቸው ደጋፊዎቻቸውን እንደጨመረላቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
ሌላኛው የቦሪስ ጆንሰን ተተኪ እጩ ጠቅላይ ሚኒስትር የህንድ ዝርያ ያላቸው እና የብሪታንያ ፋይናንስ ሚንስትር የሆኑት ሪሺ ሱናክ ምርጫውን አሸንፈው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ከሆኑ በቻይና ላይ ማዕቀቦችን እንደሚጥሉ ተናግረዋል።
ሪሺ ሱናክ ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሁለት ወራት በኋላ በሚካሄደው በቡድን 20 ጉባኤ ላይ እንዳይሳተፉ እገዳ ሊተላለፍባቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ነገ በሚያደርገው ሚስጢራዊ የድምጽ አሰጣጥ መሰረት ቦሪስ ጆንሰንን የሚተኩት ጠቅላይ ሚንስትር የሚያሳውቁ ሲሆን ተመራጩ ወይም ተመራጯ ጠቅላይ ሚኒስትር በሀገሪቱ ምክር ቤት ቃለመሀላ ፈጽመው ስራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።