አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን 1 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ በጊዜያዊነት አቆመች
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ የድጋፉ መቋረጥ “ቴክኒካዊ መዘግየት ነው” ብለዋል
አሜሪካ፤ እስራኤል የሮኬቶች ጥቃት አምካኝ ቴክኖሎጂ እንድታሳድግ እስካሁን የ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች
አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን 1 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ በጊዜያዊነት አቆመች፡፡
አሜሪካ ወታደራዊ ድጋፉን ያቆመችው በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ከሊበራል ዴሞክራቶች ተቃውሞ መነሳቱን ተከትሎ ነው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ዴሞክራቶች ለእስራኤል ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍና ድጎማ እንዲኖር የሚፈቅደውን ድንጋጌ መቃወማቸው፤ እስራኤል የ“አይረን ዶም” ሚሳኤል መከላከያ ስርዓትን /ሮኬቶችንና መሰል ጥቃቶች አየር ላይ ማምከን የሚችል ቴክኖሎጂ/ ማደስ እንድትችል ከማድረጉ በሻገር የአሜሪካው ሬይተን ኮርፖሬሽን ብዙ የብረት ዶም ግብአቶች እንዲያመርት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ምክር ቤቱ እስከ ታህሳስ 3 ቀን ድረስ ለፌዴራል መንግስቱ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እና የሀገሪቱን የብድር ወሰን ለማሳደግ በሚያስችል ሕግ ላይም ተወያይቷል።
ውሳኔው የምክር ቤቱ ኮሚቴ አባላት በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ከመከላከያ ወጪ ሂሳብ ውስጥ ለእስራኤል የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ለማካተት ቃል ከመግባታቸው በፊት ለአጭር ጊዜ እንዲዘገዩ የሚያስገድድ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ውሳኔው በአሜሪካ እና እስራኤል መካከል መቃቃር እንዳይፈጥር ከወዲሁ ተሰግቷል፡፡
የዴሞክራቶቹ ተወካይ ጀማል ቦውማን በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ለመወያየት በቂ ጊዜ አልነበረም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
“ችግሩ አመራሩ አንድ ነገር በጠረጴዛችን ላይ ይወረውራል፤ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ውሳኔ እንዳናሳልፍ ይፈልጋል፤ እኛ ግን ጉዳዩን በቀጣይ እንድንምክርበት ወስነናል” ብሏል፡፡
የአሜሪካ ኮንግረስ የምርምር አገልግሎት ሪፖርት እንደሚመላክተው ከሆነ እስራኤል ያላትን ባለብዙ ተልዕኮ ተንቀሳቃሽ የአየር መከላከያ ስርዓት /Iron Dome system/ እንድታሳድግ እስካሁን ከአሜሪካ የ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝታለች፡፡
ይህ በከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የታጀበ ትብብር ዴሞክራቶችም ሆነ ሪፓብሊካኖች ለእስራኤል የሚያደርጉትን ጠንካራ ድጋፍ የሚያመላክት ነው ተብሎለታል፡፡
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ የድጋፉ መቋረጥ “ቴክኒካዊ መዘግየት ነው” ብለውታል፡፡
የዴሞክራት ተወካዮች የድጋፍ ገንዘቡ በቅርቡ እንደሚለቁት አረጋግጠውሉኛልም ነው ሚኒስትሩ ያሉት፡፡
አንዳንድ ሊበራል ዲሞክራቶች በዚህ ዓመት የአሜሪካ-እስራኤል ፖሊሲ ሲቃወሙ ተስተውለዋል፡፡
ይህም ባለፈው ወርሃ ግንቦት ሃማስ በእስራኤል ላይ የሰነዘረውን የሮኬት ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ በበርካታ የፍልስጤም ዜጎች ላይ ከባድ ጉዳቶች ከመድረሱ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ይነሳል፡፡
እስራኤል በወቅቱ ከጋዛ ከተተኮሱባት 4 ሺህ 350 ሮኬቶች በርካቶችን እንዳመከነች መግለጿ ይታወሳል፡፡