ብሪታንያ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ ወደ 3 ነጥብ 19 ቢሊየን ዶላር አሳደገች
ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በዩክሬን ድንገተኛ ጉብኝት ሲያደርጉ 200 ሚሊየን ፓውንድ የሚያወጡ ድሮኖችን ለኬቭ እንደሚልኩ ቃል ገብተዋል
ብሪታንያና ዩክሬን ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን የሚያሳድግ “ታሪካዊ” ስምምነት ይፈራረማሉ
ብሪታንያ በቀጣዩ አመት ለዩክሬን የ3 ነጥብ 19 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ወስናለች።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በኬቭ ድንገተኛ ጉብኝት ሲያደርጉ ነው ለንደን በየአመቱ ለኬቭ የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ በ200 ሚሊየን ፓውንድ ማሳደጓን የተናገሩት።
ወታደራዊ ድጋፉ የዩክሬንን ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች፣ የአየር መቃወሚያ ስርአት እና ተተኳሽ ጥይት ክምችት የሚያሳድግ ነው ተብሏል።
ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ፓውንድ (3 ነጥብ 19 ቢሊየን ዶላር) ድጋፉ ውስጥ 200 ሚሊየን ፓውንዱ ብሪታንያ ሰራሽ ድሮኖችን ለኬቭ ለማቅረብ ይውላል መባሉንም ቢቢሲ ዘግቧል።
ይህም ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ወዲህ ከፍተኛው የድሮን ድጋፍ ይሆናል ነው የተባለው።
ከ15 ወራት በኋላ በዩክሬን ሁለተኛ ጉብኝታቸውን እያደረፉጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ፥ “ዛሬ እዚህ (ኬቭ) የተገኘሁት አንድ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፤ ብሪታንያ በዩክሬን የጨለማ ጊዜም ከጎኗ መቆሟን ለማረጋገጥ” ሲሉ ተናግረዋል።
ሀገራቱ በዛሬው እለት ታሪካዊ የደህንነት ስምምነት እንደሚፈራረሙና በሺዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን ሀገራቸው ወደ ለኬቭ እንደምትሰጥም ነው የገለጹት።
የብሪታንያ ድጋፍ ከአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ልታገኝ የነበረው ግዙፍ ወታደራዊ ድጋፍ ለተጓተተባት ኬቭ ትልቅ ብስራት ሆኗል።
አሜሪካ ለዩክሬን የ60 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ያቀረበችው ሃሳብ በአሜሪካ ደቡባዊ ድንበር የሚታየውን የስደተኞች ጎርፍ ለማስቆም ቅድሚያ ትኩረት እንስጥ ባሉ ሪፐብሊካኖች ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረትም ለኬቭ ያዘጋጀው የ50 ቢሊየን ዩሮ የድጋፍ ማዕቀፍ በሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ተቃውሞ ሳይጸድቅ መቅረቱ አይዘነጋም።