የዓለም ምግብ ፕሮግራም፤ የህወሓት ከመጋዘን የዘረፈውን ነዳጅ “አሁኑኑ መመለስ አለበት” አለ
የተመድ ቃል አቀባይ ህወሓት መቀሌ ከሚገኝ መጋዘን ነዳጅ መዝረፉን ተናግረዋል
አሜሪካም ህወሓት በመቀሌ የተመድ መጋዘን ላይ የፈፀመውን ዝርፊያ አውግዛለች
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ህወሓት በመጋዘን ውስጥ የሚገኝና ችግር ላለባቸው ዜጎች ሊከፋፈል የነበረን ነዳጅ መዝረፉን አስታወቀ።
የፕሮግራሙ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤዝሌይ “የትግራይ ባለስልጣናት” 570 ሺ ሌትር ነዳጅ ከመጋዘን መውሰዳቸውን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ነዳጅ ከሌለ በትግራይ ክልል ችግር ላይ ላሉ ወገኖች ምግብ ማድረስ እንደማይቻልም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
“የትግራይ ባለስልጣናት” የፈጸሙት አሳዛኝና ክበረ ነክ የሆነ ድርጊት እንደሆነ የገለጹት ዴቪድ ቤዝሌይ ባለስልጣናቱ የወሰዱትን ነዳጅ አሁኑኑ መመለስ አለባቸው ብለዋል።
ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፈም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህወሃት ባለስልጣናት መቀሌ ከሚገኙ የዓለም የምግብ ድርጅት መጋዘኖች ውስጥ ነዳጅ መዝረፋቸውን ገልጸዋል።
የዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬስ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በመቀሌ የህወሃት ባለስልጣናት ነዳጅ መዝረፋቸውን ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ሊከፋፈል የነበረ 570 ሺ ሊትር ነዳጅ የያዙ 12 የነዳጅ ታንከሮችን መዘረፋቸውን ነው የተመድ ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ የተናገሩት።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአፍሪካ ቢሮ ባወጣው መግለጫ፥ ታጣቂ ቡድኑ ትናንት ጠዋት ላይ መቀሌ ወደሚገኘው የድርጅቱ መጋዘን በሀይል በመግባት 12 የነዳጅ ቦቴዎችን በአጠቃላይ 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉ ዋሽንግተንን እንዳሳሰባት ጠቁሟል።
የነዳጅ ምርቱ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የነብስ አድን ቁሳቁሶች ለማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ነው መግለጫው የጠቆመው።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ለወራት ቆሞ የነበረውን ጦርነት መጀመሩን ባወጡት ትናነት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ህወሓት ባወጣው መግለጫ መከላከያ ሰራዊትና እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኃይሎች ትግራይ ደቡባዊ አቅጣጫ ባለው ግንባር በኩል ተኩስ መክፈታቸውን አስታውቋል።
የህወሓት መግለጫን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በዛሬው እለት ጠዋት 11 ሰዓት በተያየ አቅጣጫ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል።
የፌደራል መንግስት በሽብርተኝነት ከፈረጀው ህወሓት ጋር ያለውን ግጭት በድርድር ለመፍታት ማስታወቁ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚደረደር መግለጹ ይታወሳል። ህወሓትም በተመሳሳይ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነበር።